ምሥጢረ ሥላሴ
ሐዋርያ ወንጌል ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “ወባሕቱ በቤተ ክርስቲያን እፈቅድ ኀምስተ ቃላተ እንግር በልብየ = ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን አምስት ቃላትን ልናገር በልቤ እሻለሁ“ ፩ቆሮ፲፬፥፲፱ እንዳለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከውቅያኖስ የጠለቀውን ከነፋስ የረቀቀውን ትምህርተ ክርስትና በክቡር ደሙ ከዋጃት ከማይነጥፍ ከክርስቶስ ኢየሱስ ቃል ምንጭነት የታመኑ ባለሟሎቹ ሐዋርያት ቀድተው እንዳስረከቧት አዕማድ በተባሉ አምስት ምሥጢራት ከምላቱ ሳይጎድል ከስፋቱ ሳይጠብ እንደ ወርቅ እንክብል በጠሩ ኅብረ ቃላት ጠቅልላ ታስተምራለች። አምስት ምሥጢራት የተባሉትም
፩. ምሥጢረ ሥላሴ ፪. ምሥጢረ ሥጋዌ ፫. ምሥጢረ ጥምቀት ፬. ምሥጢረ ቍርባን ፭. ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ናቸው።
ዓምድ ማለት ሙሰሶ ማለት ነው፥ አዕማድ በብዙ ፤ አዕማድ መባላቸው ሙሰሶ ቤትን ማዕበል እንዳይጥለው ነፋስ እንዳይገፋው እንደሚያጸና እኒህም ልቡናን በኑፋቄ እንዳይታወክ ከክህደት ከቀቢጸ ተስፋ እንዳይደርስ በእምነት በተስፋ የሚያጸኑ ስለሆኑ ነው። ሙሰሶ የሌለው ቤት ነፋስ ሲገፋው ይወድቃል ትምህርተ ሃይማኖትም ተምሮ ያላወቀ ሰው በጥርጥር በክህደት በሃይማኖት ከሚገኝ ጸጋና ክብር ይወጣል። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ከሁሉ አስቀድማ ለወጣንያን ለማዕከላውያን በሚረዳቸው መጠን እኒህን ምሥጢራት ታስተምራለች። ምሥጢራት መባላቸውም ምሥጢር ለታመነ እንጂ ለሁሉ እንደማይነገር በክርስቶስ አምላክነት ወደማመን ለመጡ እንጂ በክህደት በአምልኮ ጣዖት ላሉ ለአሕዛብ ለአረማውያን የሚነገሩ ቢነገሩም በምር የሚረዱ ስላይደሉ፤ ዳግመኛም ለአእምሮ የረቀቀ ነገር ግን እውነት መሆኑ የታመነ ዕፁብ ዕፁብ ተብሎ በዕፁብ የሚወሰን በኅሊና መመራመር ግን የማይወሰን ድንቅ የሆነው ሁሉ ምሥጢር እንዲባል ሰው ዕፁብ ዕፁብ ብሎ በማመን የሚቀበላቸው እንጂ በመመራመር የማይወስናቸው ድንቅ እውነታዎች ስለሆኑ ነው።
በዚህ ዝግጅት ሁሉንም መዳሰስ ስለማይቻል አራቱን እግዚአብሔር ለቆረጠላቸው ጊዜ አቆይተን የመጀመሪያውን ክፍል ምሥጢረ ሥላሴን አጠር አድርገን እንመለከታለን ከሁሉ አስቀድመው ሊማሩት የሚገባም ስለሆነ። “መቅድመ ኵሉ ንሰብክ ሥላሴ ዕሩየ = ከሁሉ አስቀድመን የተካከለ ሦስትነትን (ሥላሴ) እንሰብካለን“ እንዳለ ባስልዮስ በሃ/አበው።
ሥላሴ ማለት ሦስት፣ ሦስትነት ማለት ነው። ይህ ስያሜ የሚያመለክተው በአንድነት በሦስትነት ሲመሰገን የሚኖር አንድ አምላክ እግዚአብሔርን ቢሆንም ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ሰፍሮ አይገኝም። ለመጀመሪያ ጊዜ የእንግሊዝኛ አቻው ትሪኒቲ “Trinity“ የወረሰውን ትሪኣስ የሚለውን ግሪክኛ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሑፎቹ ውስጥ የተጠቀመው በ2ኛው ክ/ዘ የነበረው ቴዎፍሎስ ዘአንጾኪያ እንደሆነ ይታመናል። ለአውግዞተ አርዮስ በ፫፻፳፭ ዓ/ም በኒቅያ የተሰበሰቡ ሃይማኖታቸው የቀና ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ቀጥሎም በ፫፻፹፩ ዓ/ም ለአውግዞ መቅዶንዮስ በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡ ፻፶ ሊቃውንት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው በተናገሩት ጸሎተ ሃይማኖት ምንም እንደ ቴዎፍሎስ ሥላሴ የሚለውን ስያሜ ባያነሡም ሥላሴ የተባሉ አብ ወልድ መንፈስቅዱስ መሆናቸውን“ነአምን በአሐዱ አምላክ እግዚአብሔር አብ አኃዜ ኵሉ ዓለም (ሁሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን).... ወነአምን በአሐዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ዋህድ (ተቀዳሚ ተካታይ በሌለው የአብ ልጅ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን)...... ወነአምን በመንፈስቅዱስ እግዚእ ማኅየዊ (ጌታ በሆነ ሕይወትንም በሚሰጥ በመንፈስቅዱስ እናምናለን)... በሚል የሃይማኖት ምስክርነት ቃል ገልጠውታል። ጸሎ.ሃይ
ይህም ትምህርት የክርስትና ትምህርት አስኳል ሲሆን ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ከመጽሐፍ ቅዱስ የተቀዳ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት እንጅ የተጠቀሱት አባቶች ከራሳቸው ያነቁት ድንገተኛ አሳብ አይደለም። አንድነት ሦስትነታቸውን እንደሚከተለው ማስረጃ ጠቅሰን እንመለከታለን።
ሥላሴ ሦስትነታቸው በስም ፣ በአካልና በግብር ሲሆን አንድነታቸው ደግሞ በባሕርይ፣ በህልውና፣በመለኮት በሥልጣንና በአገዛዝ ነው።
የስም ሦስትነት፡.. አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ይባላሉ።
ማስረጃ- “ወእንዘ ታጠምቅዎሙ በሉ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ = ስታጠምቋቸውም በአብና በወልድ በመንፈሳዱስም ስም በሉ“ማቴ፳፰፥፲፱
“ጸጋሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወፍቅረ እግዚአብሔር ወሱታፌ መንፈስቅዱስ የሀሉ ምስለ ኵልክሙ = የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔር ፍቅር የመንፈስቅዱስ አንድነት ከሁላችሁ ጋር ይሁን“ ፪ቆሮ፲፫፥፲፬
የአካል ሦስትነት፡ ለአብ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክእ አለው፤ ለወልድም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክእ አለው፤ ለመንፈስቅዱስም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክእ አለው። ሃ/አበ ዘአቡሉዲስ
አካል፡ ከራስ ጸጕር እስከ እግር ጥፍር ያለው ነው፤ ገጽ ፊት ነው ፤ መልክእም ከራስ ፀጕር እስክ እግር ጥፍር ድረስ ያለው ነው። አካልም እንዳላቸው ከሚያስረዱ ማስረጃዎች ጥቂቶቹን እንደሚከተለው እናያለን።
ማስረጃ - “ይቤ እግዚአብሔር ንግበር ሰብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ = እግዚአብሔርም አለ ሰውን እንደ መልካችንና እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር“ ዘፍ ፩፥፳፮
“ወአፄነወ እግዚአብሔር መዓዛ መሥዋዕቱ ለኖህ = እግዚአብሔርም የኖኅን የመሥዋዕቱን መዓዛ አሸተ“ ዘፍ፰፥፳፩
“ወጾሮሙ በእንግድዓሁ እግዚአብሔር ባሕቲቱ መርሖሙ = በደረቱም አቀፋቸው እግዚአብሔር ብቻውን መራቸው“ ዘዳ ፴፪፥፲፩
“እስመ አዕይንቲሁ ለእግዚአብሔር ኀበ ጻድቃኑ ወእዝኑሂ ኀበ ስእለቶሙ = የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃኑ ናቸው ጆሮውም ወደልመናቸው“ መዝ ፴፫፥፲፭
“ዮድ እደዊከ ገብራኒ ወለሐኳኒ = ዮድ እነሆ እጆችህ ሠሩኝ አበጁኝም“ መዝ፻፲፰፥፸፫
“ወንሰግድ ውስተ መካን ኀበ ቆመ እግረ እግዚእነ = የእግዚአብሔር እግር በቆመበት ሥፍራ በዚያ እንሰግዳለን“ መዝ ፻፴፩፥፯
“ሰማይኒ መንበርየ ወምድርኒ መከየደ እገርየ = ሰማይ መቀመጫዬ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት“ ኢሳ ፷፮፥፩
“ዘሰ አምነኒ በገጸ ሰብእ አነኒ አአምኖ በገጸ አቡየ ዘበሰማያት = በሰው ፊት የሚያምንብኝን እኔም እሱን በአባቴ ፊት አምነዋለሁ“ ማቴ ፲፥፴
ዳግመኛም ለአብርሃም በመምሬ አድባር ዛፍ ሥር በሦስት ጎልማሶች አምሳል ተገልጸዋል። ለዮሐንስም በዮርዳኖስ አብ በደመና ሆኖየምወደው ልጄ ይህ ነው ሲል ወልድም በማየ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ መንፈቅዱስም በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲያርፍ በሦስት አካላት ተገልጸዋል። ዘፍ ፲፰፥፲፬ ማቴ፫፥፲፮
የግብር ሦስትነት፡ የአብ ግብሩ መውለድ ማሥረጽ ፤ የወልድ ግብሩ መወለድ የመንፈስቅዱስ ግብሩ መሥረጽ ነው። አብ ቢወልድ እንጂ እንደ ወልድ አይወለድም እንደመንፈስቅዱስ አይሠርጽም፤ ወልድም ቢወለድ እንጂ እንደ አብ አይወልድም አያሠርጽም እንደ መንፈስቅዱስ አይሠርጽም፤ መንፈስቅዱስም ቢሠርጽ እንጂ እንደ አብ አይወልድም አያሠርጽም እንደወልድም አይወለድም። ሃ/አበ ዘቴዎ
ይህም ግብራቸው ዕፁብ ዕፁብ ተብሎ በዕፁብ ይወሰናል እንጂ አይመረመርም “ልደተ ወልድ ወጸአተ መንፈስቅዱስ እምኀበ ኢይትነገር አላ ይትነከር = የወልድ መወለድ የመንፈስቅዱስም መሥረጽ በመናገር የሚፈጸም አይደለም ይደነቃል እንጂ“ እንዲል ሃ/አበ ዘዲዮ
አብን ወላዲ ወልድን ተወላዲ መንፈስቅዱስን ሠራፂ ስላልን ግን የሚበላለጡ አይደሉም አንድ ናቸው። “ኢይልህቅ አብ እምወልዱ ወልድኒ ኢይልህቅ እመንፈስቅዱስ ወመንፈስቅዱስኒ ኢይንዕስ እምወልድ ወወልድኒ ኢይንዕስ እም አቡሁ = አብ ከልጁ አይበልጥም ወልድም ከመንፈስቅዱስ አይበልጥም መነፈስቅዱስም ከወልድ አያንስም ወልድም ከአባቱ አያንስም“ እንዲል ቅ/ማር ቁ.፶፭
ጌታም መተካከላቸውን ሲያጠይቅ “አነ ወአብ አሐዱ ንሕነ = እኔና አባቴ አንድ ነን“ ብሏል ዮሐ፲፥፴
እንዲህም ማለት ሦስት አማልክት ማለት አይደለም አንድ አምላክ ይባላሉ እንጂ “ወመለኮትሰ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ= መለኮት ግን አምላክ አብ ወልድ መንፈስቅዱስ ነው“ እንዳለ አባ ሕርያቆስ። ቅ/ማር ቁ.፶፯ በግብር ሦስት በአምላክነት አንድ የመሆናቸውን ነገር በፀሐይ በእሳት መስለው ያስረዳሉ። ፀሐይ ክበብ፣ ሙቀት፣ ብርሃን፤ እሳትም ነበልባል፣ ፍሕም፣ ሙቀት፣ አላቸው ነገር ግን አንድ ፀሐይ አንድ እሳት ቢባሉ እንጂ ሦስት ፀሐይ ሦስት እሳት አይባሉም። እንደዚሁ ሥላሴም በአካል በግብር በስም ሦስት ቢባሉም ቅሉ አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አይባሉም። “ስማዕ እስራኤል አሐዱ ውእቱ አምላክከ እግዚአብሔር = እስራኤል ሆይ ስማ አምላክህ እግዚአብሔር አንድ ነኝ“። ዘጸ ፳፥፩
የአንድነታቸውስ ነገር እንደምን ነው ቢሉ በባሕርይ፣ በህልውና፣ በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ አንድ ናቸው። የህልውና አንድነታቸው፡ በአብ ልቡናነት ወልድ መንፈስቅዱስ ህልዋን ናቸው ያስቡበታል፤ በወልድ ቃልነት አብ መንፈስቅዱስ ህልዋን ናቸው ይናገሩበታል፤ በመንፈስቅዱስ እስትንፋስነት አብ ወልድ ህልዋን ናቸው ይተነፍሱበታል “አሐዱ ህላዌሆሙ ለሥላሴ እንዘ ይሄልዉ በበአካላቲሆሙ ወዕሩያን እሙንቱ በህልውና አብኒ ልቦሙ ለወልድ ወለመንፈስቅዱስ ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ወለመንፈስቅዱስ ወመንፈስቅዱስኒ እስትንፋሶሙ ለአብ ወለወልድ= ለየራሳቸው አካል ሳላቸው የሥላሴ ህልውና አንድ ነው : በህልውና የተካከሉ ናቸው:: አብ ለወልድና ለመንፈስቅዱስ ልባቸው ነው ወልድም ለአብና ለመንፈስቅዱስ ቃላቸው ነው፤ መንፈስቅዱስም ለአብና ለወልድ እስትንፋሳቸው ነው“ እንዲል ሃ/አበ ዘአቡሊዲስ።
ምሥጢረ ሥላሴ የሚባለው ከረጅሙ ባጭሩ ከብዙ በጥቂቱ ይህ ከዓለማት መፈጠር አስቀድሞ በአንድነት በሦስትነት ሲመሰገን የነበረ አሁንም ያለ ዓለማትንም አሳልፎ በአምላክነቱ ግብር ጸንቶ የሚኖር ጌታ እግዚአብሔርን አንድም ሦስትም የሚባልበትን ምሥጢር የሚማሩበት ትምህርት ነው። የሃይማኖት ጥንቱ መሠረቱ እግዚአብሔርን ማመን ነውና የሚያምኑት እግዚአብሔር ስሙ ባሕርዩ ግብሩ ምን እንደሚመስል መማር ማወቅ የምእመናን ሁሉ ኃላፊነት ነው። ይህን ጠንቅቀው ካወቅን ዘንድ ወልድ ፍጡር ያለ አርዮስንና ትምህርቱን፤ መንፈስቅዱስ ሕጹጽ ያለ መቅዶንዮስንና ክህደቱን ሌሎቹንም መናፍቃንንና ኑፋቄ ያለበት አሰተኛ ትምህርታቸውን እየተቃወምን የሰይጣንን ምክሩን እናፈርሳለን የምናምነውን አምላክም አዕምሮአችን ማወቅ የሚቻለው ድረስ ዐውቀነው በአገባብ እናመልከዋለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ