ሐሙስ 26 ፌብሩዋሪ 2015

ኢየሱስ ፈራጅ ወይስ አማላጅ?
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን፡፡
በእኔ የማይሰናከል ሁሉ ብፁዕ ነው፡፡ ማቴ. 11፡6 ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው የእጁን ተዐምራትና የቃሉን ትምህርት እየተመለከቱ ወልደ ዮሴፍ እሩቅ ብዕሲ(የዮሴፍ ልጅ ተራ ሰው) ይሉት ለነበሩት አይሁድ በእኔ የማይሰናከል ሁሉ ብፁዕ ነው አላቸው በወቅቱ ግን ልብ ያላሉ አይሁድ ጌታችን የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር መሆኑን ሲነግራቸው ሊወግሩት ድንጋይ ይፈልጉ ነበር በተሰቀለ ጊዜም የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ይላል እራሱን ግን ከመስቀል ማዳን አይችልም ብለው ያሾፉበት ነበር፡፡ ዛሬም ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ኃይለ ቃላትን እየመዘዙ በኢየሱስ ክርስቶስ እየተሰናከሉ ያሉ ብዙዎች ናቸው ከነዚህም መካከል ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነው ብለው የተሰናከሉት ይበዛሉ፡፡ ቤተክርስቲያናችን ለእነዚህ ሰዎች በዚህ ጽሑፍ መልስ ትሰጣለች ሁሌም እንደምንለው ስለመማማር እንጂ ስለክርክር አይደለም፤ ስለፍቅር እነጂ ስለ ፀብ አይደለም፤ ስለመዋደድ እንጂ ስለ ጥላቻ አይደለም፡፡
አማላጅ ማለት አንድን ሰው ወክሎ ወይም የአንድን ሰው ልመና ይዞ በአምላክ ፊት የሚቀርብ ማለት ነው፡፡ በተለይም ከድካማችን የተነሳ ህሊናችን በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም ስለማይችል አማላጅ እንፈልጋለን፡፡
በዚህ ፍቺ ከተስማማን አማላጅ ማነው የሚለውን ከመመለሳችን በፊት ምልጃው የሚቀርብለት አምላክ ማነው የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
እዚህ ላይ ግን ቤተክርስቲያናችን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ብላ እንደምታምን መዘንጋት የለብንም ሆኖም ይህ ጽሁፍ ዋና አላማው ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ ፈራጅ ወይስ አማላጅ የሚለውን ለመመለስ በመሆኑ ትኩረቱን ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያደርጋልና ይህ ሲሆን ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ ብቻውን አምላክ ነው ማለት እንዳልሆነ በልቦናችን እናሳድር፡፡
ሮሜ. 9፡5 አባቶች ለእነርሱ ናቸውና ከእነርሱም ክርስቶስ በስጋ መጣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ የተባረከ አምላክ ነው አሜን፡፡
1ኛ ዮሐ.5፡20 የእግዚአብሔርም ልጅ እንደመጣ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው፡፡
እንግዲህ ምልጃ የሚቀርበው ወደ አምላክ ነው ካልን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ አምላክ እንደሆነ ካመንን ያለ አንዳች መጠራጠር ምልጃው የሚቀርበው ወደ እርሱ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ እንረዳለን እናምናለን፡፡
እናም ጥያቄውን በቀጥታ ለመመለስ ቤተክርስቲያናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጅ እንጂ አማላጅ አይደለም ትላለች፡፡ ከላይ በየክፍሉ የተዘረዘሩትንና ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጅ በሚሉ ሰዎች እንደማስረጃ የሚቀርቡትን ጥቅሶች እያንዳንዱን በተናጠል እያየን መልስ የምንሰጥበት ይሆንና በዚህ ክፍል ግን ኢየሱስ ክርስቶስን ፈራጅ እንጂ አማላጅ አይደለም የምንልበትን ምክንያት በማስረጃ እንመልሳለን
ለምን አይማልድም?
ከዚህ በፊት በጻፍነው ጽሕፍ ላይ የመናፍቃን ታላቁና መሰረታዊው ስህተታቸው ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ነጥለውና ገንጥለው ማየታቸው እንደሆነ ገልፀናል አሁንም ወልድ አማላጅ ነው ለማለታቸው መሰረቱ ይህ አስተሳሰባቸው ነው እዚህ ላይ ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን እንይዛለን
1. አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመፍጠር፣ በመግዛት፣ በስልጣን፣ በማድረግና ባለማድረግ ፍፁም አንድ ናቸው ብሎ ማመን
2. የመለኮትና የትስብዕትን ፍፁም ተዋህዶ ማመን
እነዚህ ሁለቱን የሚያምን እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊ በመሆኑ በምንም ተዐምር ጥራዝ ነጠቅ ጥቅስ ይዞ ኢየሱስ አማላጅ ነው አይልም፡፡ በተራ ቁጥር 1 ላይ ያለውን ባለማመናቸው በጥራዝ ነጠቅ ጥቅስ እየሳቱ ያሉት የዘመናችን መናፍቃን ሲሆኑ በተራ ቁጥር 2 ላይ ያለውን ባለማመን የሚስቱት ደግሞ የምስራቅ/ኢስተርን/ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተክርስቲያናት ናቸው እነዚህ እንዴት እንደሳቱ በክፍል ሁለት ላይ የምንመለከተው ይሆናል ለዛሬ ግን የዘመናችን መናፍቃን የሳቱበትን ተራ ቁጥር 1 እንመልከት
በእርግጥ እነሱን ብንጠይቃቸው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ መሆናቸውን እናምናለን ይሉናል ግን ደግሞ እምነታቸው አለማመናቸውን ነው የሚነግረን እንዴት ቢባል ለምኖ የሚያሰጥና ተለምኖ የሚሰጥ አንድ አይደለምና እነሱ የሚያምኑት ወልድን አማላጅ(ለምኖ የሚያሰጥ)መሆኑን ሲሆን አብና መንፈስ ቅዱስ ግን የሚሰጡ እንጂ የማይለምኑ መሆናቸውን ነው ይህም ማለት ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ ይለምናል ብለው ያምናሉ ማለት ነው ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ማንም ህሊና ያለው ቢመዝነው ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ያንሳል እንደማለት ይቆጠራል ሎቱ ስብሀት፡፡ ሦስቱም አንድ መሆናቸውን የሚያምን ማንም ቢኖር ሁለት አማራጭ ብቻ ነው ያለው አንድም አብ ወልድ መንፈስቅዱስ ሦስቱም ያማልዳሉ ማለት ካልሆነም አብ ወልድ መንፈስቅዱስ ሦስቱም ይፈርዳሉ እንጂ አያማልዱም ብሎ ማመን ከዚህ ውጪ እያመኑ ግን እኩል ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ እንግዲህ ይህን በማስረጃ ለማየት እንሞክራለን፡-
ዮሐ.5፡19- እውነት እውነት እላችኋለሁ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና፡፡
ወልድ የሚያደርገው አብ የሚያደርገውን ነውና ወልድ አማላጅ ነው ካልን አብም አማላጅ ነው ማለት ይሆንብናል፡፡
ፊል. 2፡11 አንደበትም ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር አብ ክብር ጌታ እንደሆነ ያምን ዘንድ ነው፡፡
አብ እና ወልድ በአንድ አይነት ክብር መሆናቸውን ካመንን አንዱ ከሌላው ተለይቶ አማላጅ ሊሆን አይችልምና ኢየሱስ አማላጅ የሚሉ አብን አማላጅ አድርገውታል፡፡
ዮሐ.5፡21-አብ ሙታንን እንደሚያነሳ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል፡፡
ወልድ ህይወትን ይሰጣቸዋል አለ እንጂ ያሰጣቸዋል አላለም ይልቁንም ክርስቶስ በስጋ ስለመጣ ብቻ ከአብ ያንሳል እንዳንል ወንጌላዊው ከአብ ጋር በማነፃፀር አስረዳን
ዮሐ.1፡30- እኔና አብ አንድ ነን
ይህ ምንም ማብራሪያ አያስፈልገውም ይልቁን ከላይ የጠቀስናቸውን ጠቅልሎ አንድነታቸውን በግልጽ ያስረዳናል፡፡
ጥቂት እንጨምርና ማሰልቸት እንዳይሆን ክፍል አንድን እናጠቃል
አማላጅ ለምኖ ያሰጣል እንጂ ሰጪ አይደለም ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሚሰጥ እንጂ የሚያሰጥ ስላልሆነ አማላጅ አንለውም
ዮሐ.1፡4 ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለርሱ የሆነ የለም፡፡
ቖላ.1፡15-16-እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው የሚታዩትና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው፡፡ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፡፡
እንግዲህ ሁሉ በእርሱ የሚሆን ከሆነ ከማን ምን ይለምን? የሁሉ አስገኝና ፈጣሪ እርሱ ከሆነ ማድረግ እንጂ መጠየቅ ስለምን ያስፈልገዋል?
በመጨረሻም እንደ ቤተክርስቲያናችን አስተምሮ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ የፈጸመው ነገር የማስታረቅ ስራ ይባላል ያንን የማስታረቅ ሥራ ግን አሁንም እየወደቀ እየተነሳ አይሰራውም ለቅዱሳኑ ሰጥቷቸዋልና
2ኛ ቆሮ 5፡18-19-ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ፡፡
ሁላችን መጽሐፍ እርስ በእርሱ እንደማይጋጭ እናምናለን ይህ ከሆነ ቅ.ጳውሎስ በግልፅ ቋንቋ ያስታርቅ ነበርና በማለት ክርስቶስ በምድር ላይ የማስታረቅን ስራ እንደሰራ "ነበርና" በሚለው በአላፊ ወይም ፍፃሜውን ያገኘ ድርጊት መሆኑን በሚገልፅ ዘይቤ ካስረዳ በኋላ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ የአፃፃፍ ዘይቤ ነው እንዳንል የማስታረቅን አገልግሎት ከሰጠን እንዲሁም በእኛ የማስታረቅ ቃል አኖረ በማለት ከዚያ በኋላ የማስታረቁን ሥራ ለእነሱ ለቅዱሳኑ እንደሰጣቸው በማያሻማ ሁኔታ ገልፆልናል፡፡
እንግዲህ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጅ እንጂ አማላጅ አይደለም ስንል መሰረታችን ይህ ነው፡፡ ታዲያ ኢየሱስን አማላጅ የሚሉት ሰዎች የሚያቀርቡአቸው ማስረጃዎችስ የሚለውን በቀጣይ በተከታታይና እያንዳንዱን በተናጠል የምናየው ይሆናል እግዚአብሔር ለሁላችን ማስተዋሉን ይስጠን ለዛሬው በዚህ ይብቃን::
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የቀደመችው እውነተኛይቱ መንገድ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ