ሐሙስ 26 ፌብሩዋሪ 2015

ትምሕርተ ሃይማኖት/ክፍል 4
አምስቱ አእማደ ምሥጢር
መግቢያ
አምስት ፤ ቁጥራቸው አምስት ብቻ ሆኖ የተወሰነው ፤ በ1 ሳሙ 17 ፥ 40 ። እና በ 1ቆሮ 14 ፥ 19 ። ባለው ቃል መሠረት ሲሆን ፤ አምስት መሆናቸውና የተደረጉባቸው ድንቅ ሥራዎች የአምስቱ አእማደ ምሥጢር ምሳሌነታቸውን ያስረዳል ።
አእማድ
አምድ ማለት ምሰሶ ማለት ሲሆን አእማድ ማለት ምሰሶዎች ማለት ነው ። ቤት በአምድ (በኮለም) እንደሚፀና ፤ ሃይማኖትም በነዚህ ምሥጢራት ተጠቃሎ ይገለጻል ፤ ምዕመናንም እነዚህን ምሥጢራት በመማር ፀንተው ይኖራሉ ።
ምሥጢር
ምሥጢር ፤ ማለት ለተወሰነ ጊዜ በተወሰኑ ሰዎች ብቻ ተጠብቆ የሚቆይ ሲሆን ፤ በዚህ ትምህርታችን ግን በሚታዩ ምሳሌዎች የማይታየውን የሃይማኖት ምሥጢር መረዳት ፤ በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ፀጋ ማግኘት ማለት ነው ።
እነዚህም ምሥጢራት
- ምሥጢረ ሥላሴ (የሥላሴን አንድነትና ሶስትነት የምንማርበት)
- ምሥጢረ ሥጋዌ (የአምላክን ሰው መሆን… የምንማርበት)
- ምሥጢረ ጥምቀት (ስለ ዳግም መወለድ.. የምንማርበት
- ምሥጢረ ቁርባን (ስለ ክርስቶስ ሥጋና ደም… የምንማርበት)
- ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን(ስለ ዳግም ምጽዓት የምንማርበት) ናቸው ።
በአፈፃፀማቸው መሰረት በሶስት ይከፈላሉ ።
. ምሥጢረ ሥላሴና ምሥጢረ ሥጋዌ አምነን የምንቀበላቸው ።
. ምሥጢረ ጥምቀትና ምሥጢረ ቁርባን አምነን በሥራ ::
. ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን አምነን በተስፋ የምንጠብቀው ።
በዘመናት አከፋፈላቸው በሶስት ይከፈላሉ ።
. ምሥጢረ ሥላሴ ቅድመ ዓለም ከዘመናት በፊት ያለውን
. ምሥጢረ ሥጋዌ
. ምሥጢረ ጥምቀት
. ምሥጢረ ቁርባን በዘመነ ሥጋዌ የሆነውን
. ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ከዓለም ፍጻሜ በኋላ የሚሆነውን ያስረዳሉ ።
ምሥጢረ ሥላሴ
ሠለሰ ሶስት አደረገ ፤ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ፤ ሥላሴ ማለት ሶስትነት ማለት ነው ። በዚህ ትምህርት የአምላክን አንድነት ሶስትነት እንማራለን ።
የምሥጢረ ሥላሴን ትምህርት በምንማርበት ጊዜ ከሂሳብ ቀመር ህግ አስተሳሰብ ውጭ ሆነን ነው ። ምክንያቱም መንሳዊዉ ሥጋዊዉን ጥበብ (ፍልስፍና) ይመረምረዋል እንጅ መንፈሳዊ ጥበብና ምሥጢር በዓለማዊ ዕውቀት ምርምር ሊደረስበት አይቻልምና ። የሃይማኖት ነገር ቁሳዊ ሳይሆን መንፈሳዊና በሃይማኖት ሆኖ በመንፈሳዊነት የሚታወቅና የሚታመ ን ነው ።
የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት በብሉይ ኪዳን
ዘፍ 1 ፥ 26 ። “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር አለ” ። ከዚህ ቃል በፊት እግዚአብሔርን የሚመስል ፍጡር መኖሩን የሚገልጽ ባለመኖሩ “በመልካችን...”የሚለው እግዚአብሔር የራሱ የሆነ ከአንድ በላይ መልክ እንዳለው ያስረዳል ። እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር ማንም እንዳላማከረውና ረዳትም እንዳላስፈለገው በኢሳ 40 ፥ 12 ። ላይ ተጽፎ እናገኛለን ። በመ ሆኑም “በመልካችን..”የሚለው ሶስትነቱን(ከአንድ በላይ መሆኑን)“አለ” የሚለው ደግሞ አንድነቱን ይገልጽልናል ።
“አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” ዘፍ 3 ፥ 22 ። እግዚአብሔር በአካልና በስምና በግብር ሶስትነት ባይኖረው ኖሮ “እንደ እኔ ሆነ” በማለት ይናገር ነበር ። “ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” የሚለው ግን ብዙ ቁጥርን አመላካች በመሆኑ እግዚአብሔር አንድ ብቻ እንዳልሆነ ያስረዳናል ።
ዘፍ 11 ፥ 7 ። “ኑ እንውረድና ቋንቋቸውን እንደባልቀው አለ” ይህ ቃል አንዱ ሌሎቹን ኑ እንደሚል እንረዳለን ። በዚህም እግዚአብሔር ለአምላክነት ሥራው የማንንም እርዳታ እንደማይፈልግ የሚታወቅ ሲሆን በውስጡ ከሁለት በላይ እንደሆነ አንዱ ሌሎቹን “ኑ” በማለቱ ያስረዳል ።
ዘፍ 18 ፥ 1 ። እግዚአብሔር በመምሬ ዛፍ ስር ለአብርሐም ተገለጠለት ። አብርሐምም ዓይኑን አነሳና ሶስት ሰዎችን አየ የሚለው እግዚአብሔር በሶስትነቱ በሰዎች አምሳል ለአብርሐም መገለጡን በቁጥር ሶሰት ብሎ ያስረዳል ። ሀሳቡን ግልጽ ለማድረግ እግዚአብሔር ከሶስት ሰዎች ጋር ወይም ከሁለት መላእክት ጋር ተገለጠለት አይልም ። መላእክትም ሆኑ ሰዎች በዚህ ሥም አይጠሩም ኢሳ 42 ፥ 8 ። እስከዚህ ድረስ ብዛትን ብቻ ሲያመልክት የነበረው በዚህ ላይ ሶስት ብሎ ለይቶ ስለተናገረ እግዚአብሔር ሶስትነት ያለው መሆኑን በግልጽ ያስረዳል ።
የእግዚአብሔር ሶስትነት ፤ እግዚአብሔር ፤ በስም ፤ በግብር ፤ በአካል ፤ ሶስት ነው ።
የስም ሶስትነት
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመባል ነው ። “ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው” ማቴ ፳፰ ፥ ፲፱ ። የአብ ፍቅር ፤ የወልድ ፀጋ ፤ የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ፤ የሚለው ቃል ሶስትነቱን በግልጽ ያስረዳል ። 2ቆሮ 13 ፥ 14 ።
ስሙ (የወልድ) ፤ የአባቱ ስም ፤ የመንፈስ ቅዱስ ስም ፤ የተጻፈባቸው ። ራዕ 14 ፥ 1 ። ከላይ የተገለጹት የእግዚአብሔርን የስም ሶስትነት ያስረዳሉ ።
አብ ፤ በራሱ ሥም አብ ይባላል እንጅ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይባልም ። ሶስቱም በየስማቸው ይጠራሉ ። ሃይ አበው ምዕ 11. ክፍል 1 ፡ 7 ።
“ሥላሴ” ማለት ሶስትነት ማለት ሲሆን ፤ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ የሶስትነት ጥቅል ስም ነው ። “ሥላሴ” በምን ልበት ጊዜ አብ ፤ ወልድ ፤ መንፈስ ቅዱስ ፤ ማለታችን ነው ።
የግብር ሶስትነት
ግብር ሥራ ማለት ሲሆን ፦ በዚህ ክፍለ ትምህርት የእግዚአብሔርን የግብር ሶስትነት (አብ አባት ፣ ወልድ ልጅ ፤ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ መሆናቸውን) እናያለን ።
አብ ማለት አባት (ወልድን የወለደ) ። ማቴ 3 ፥ 17 ። አስራጺ መንፈስ ቅዱስን ያሰረጸ (ያስገኘ) ። ዮሐ 15 ፥ 26 ።
ወልድ ፤ ተወላዲ (ከአብ የተወለደ) ። ሉቃ 1 ፥ 35 ።
መንፈስ ቅዱስ ማለት ፤ ሰራጺ (ከአብ የሰረጸ) ። ዮሐ ፲፭ ፥ 26 ። ማለት ነው ።
የግብር ሶስነቱ የስሙን ሶስትነት ይገልጻል ። አብ አባት ፣ ወልድ ልጅ ፣ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ (ሕይወት)፣ በማለት ። ይህ ማለት ግን አብ አባትና አስገኝ ፣ ስለተባለ ከአብና ከወልድ አይቀድምም አይበልጥም ፤ ወልድም ከአብ አያንስም ፤ ከመ ንፈስ ቅዱስ አያንስም ፤ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ከወልድ አያንስም ። ሁሉም እኩል በአንድነትና በሶስትነት ይመሰገናሉ ።
የአካል ሶስትነት
ለአብ ፣ ለወልድ ፣ ለመንፈሰ ቅዱስ ለየራሳቸው ፍፁም (ሙሉ) ገጽ ፣ ፍፁም መልክ ፣ ፍፁም አካል ፣ አላቸው ።
ገጽ ፊት ማለት ሲሆን ፣ ከአንገታችን በላይ የሚታዩት የሰውነት ክፍሎቻችንን ዓይን ፣ ጆሮ.... የመሳሰሉትን ያጠቃልላል ።
መልክ በእያንዳንዳቸው የሰውነታችን ክፍሎች (እግር ፣ እጅ ፣ ራስ ፣ ፀጉር ፣ ዓይን ፣ ጆሮ…..) ተብለው ሲቆጠሩ ነው ።
አካል በአጠቃላይ ሙሉው የሰውነታችን ክፍል ነው ። የፍጡራን አካል የሚታይ ፣ የሚዳሰስ ፣ የሚመጠን ፤ የሚወሰን ፣ ሲሆን የሥላሴ አካል ግን ፤ የማይታይ ፣ በእጅ የማይዳሰስ ፣ በቦታ የማይወሰን ፣ በሁሉም ሙሉ ነው ። መዝ 138 ፥ 7 ።
የእግዚአብሔር የአካል ሶስትነት ። በማቴ 3 ፥ 16 ። እንደተገለጠው አብ በደመና ፣ ወልድ በለበሰው ሥጋ ፣ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በመሆን በግልጽ ታይቷል ። በሌላም በኩል ለአብርሐም በሶስት ሰዎች አምሳል የተገለጠለት ፣ በአካል ሶስት መሆኑን ሲያስረዳው ነው ። የሥላሴ ሶስትነት ከሰዎች የሂሳብ ቀመር ልዩ ስለሆነ (ቅድስት ሥላሴ) ልዩ ሶስትነት ይባላል ። በሂሳብ ህግ አንድ ሲሆን ሶስት…. የሚሆን ነገር የለምና ። የየራሳቸው የሶስትነት ፣ ሥም ፣ ግብር ፣ አካል ፣ አላቸው ።
የእግዚአብሔር አንድነት
የእግዚአብሔር ሶስትነት በሶስት ነገሮች በስም ፣ በግብር ፣ በአካል ፣ ብቻ ሲሆን በሌላው ሁሉ ለምሳሌ በባህርይ በህልውና ዮሐ 14 ፥ 8 ። በፈቃድ ፣ በሥልጣን ፣ በመፍጠር… ፣ አንድ ነው ። ለአብ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ በተለያየሥራና ደረጃ ተጽፎ ብናገኝም የስማቸውን የግብራቸውንና የአካላቸውን ሶስትነት ለመግለጽ እንጅ በአንዱ ሥራ ሁሉም አሉበት ። ዓለምን ፈጥሮ እየገዛ ያለ ፣ ሰው ሆኖ ዓለምን ያዳነ ፣ አምላክ አንድ ብቻ ነው ። ኤፌ 4 ፥ 5 ።
ኩነት (ከዊን)
ኩነት ወይም ከዊን ማለት ሁኔታ ወይም መሆን ማለት ሲሆን ፣ ይህም በሰው ነፍስ ምሳሌ ይገለጻል ። ነፍስ አንዲት ስትሆን ሶስት ባህርያት (ኩነታት) አሏት ፤ እነሱም ፤ ልብ (ማሰብ) ፤ ቃል (መናገር) ፤ እስትንፋስ (ሕይወት) ናቸው ። ከሶስቱ ባህር ያት አንዱ ከተጓደለ ነፍስ የሚለውን ስም ልታገኝ አትችልም ።
የእግዚአብሔር ሶስትነት በሰው ነፍስ ምሳሌ ሆኖ ቀርቧል ። ይኸውም አብ በልብ (ማሰብ) ፣ ወልድ በቃል (መናገር) ፣ መን ፈስ ቅዱስ በእስትፋስ (ሕይወት) ሲሆን አብ ለራሱ ልብ ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው ። ወልድም ለራሱ ቃል ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው ። መንፈስ ቅዱስም ለራሱ ሕይወት ሆኖ ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው ነው ። በእግዚአብሔርነቱ ፤ ልብ ፣ ቃል ፣ ሕይወት አለ ። ነፍስ ሶስት ባህርያት ቢኖሯትም አንድ እንደምትባል እግዚአብሔርም ሶስት ስም ፤ ሶስት ግብር ፤ ሶስት አካል ፤ ቢኖረውም አንድ አምላክ እንጅ ሶስት አማልክት አይባልም ። ዘዳ 6 ፥፬ ። ሚል 2 ፥ 10 ።
የእግዚአብሔርን አንድነትና ሶስትነት ለማስረዳት የቀረቡ ምሳሌዎች
ፀሀይ
አካል (መጠን) ብርሃን ሙቀት አላት ። በአካሏ አብ ፣ በብርሃኗ ወልድ ፣ በሙቀቷ መንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሆነው ቀርበዋል ። ፀሀይ ሶስት ሁኔታዎች ሲኖሯት አንድ እንደሆነች እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ሶስት ፤ ሶስት ሲሆን አንድ አምላክ ነው ።
ውሃ
ይዘት(ስፋት) ፣ እርጥበት ፣ ቅዝቃዜ አለው ። በይዘቱ (በስፋቱ) አብ ፣ በእርጥበቱ ወልድ ፣ በቅዝቃዜው መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ ። ውሃ አንድ እንደሆነ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ሶስት ፤ ሶስት ሲሆን አንድ አምላክ ነው ።
ሌሎቹም በምሳሌነት የሚቀርቡ ፍጥረታት አሉ ። ነገር ግን በምሳሌነታቸው ለማስተማር እንጅ የአምላክን ባህርይ የፍጡር ባህርይ ሊያስረዳ አይችልም ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ