ማክሰኞ 17 ማርች 2015





 
 ‹‹እርሱም መልሶ፦ ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ።››
                የማቴዎስ ወንጌል 15፡24/ይድረስ ለአህዛብ/
ብዙ ጊዜ መሀመዳውያን ይህንን የጌታችንን ንግግር በመያዝ ኢየሱስ የተላከው ለእስራኤላውያን ብቻ ነው ይላሉ እስቲ አብረን ጥቅሱን እንመልከተው፡-
በመጀመሪያ ደረጃ እስራኤል ማለት ኤሁዳውያን ብቻ አይደሉም እኛ የሀዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች እስራኤል ዘነፍስ ተብለን እንጠራለን፡፡ከእስራኤል ቤት የጠፉት በጎች ሲል ጥቁስን ብቻውን ከወንጌላቱ የታሪክ አውድ (context)ነጥለን ስናነብበው፤ ከእስራኤል ወገን የሆኑ ሌሎች የጠፉ ነገዶች ወይም ዘሮች ያሉ ሊያስመስል ይችላል። ነገር ግን የትም ቦታ ኢየሱስ ከእስራኤል ለሆነ አንድ የጠፋ ነገደ ወዘተ ነው የተላኩት የሚል ነገር ተናግሮ አያውቅም፤ ይህንንም ሲያደርግ አይታይም። እንዲህ ያለ የተሳሳተ ሃሳብ፤ ማለትም ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ አንዱን ነጥሎ ኢየሱስ የፈለገበት ወዘተ ነገር በወንጌላቱ አንድም ቦታ የለም። ብዙ ጊዜም ጥቅስን ብቻ ከአውዱ(context) መነጠል አደጋው እዚህ ላይ ነው። ጨርሶ absurd ወደሆነ መደምደሚያ እንድንደረስ ያደርገናል።

ነገር ግን ይህን ክፍል ጥቅሱን ብቻውን ነጥለን ሳይሆን ከጠቅላላው የወንጌላቱ ታሪክ ጋር ስንመለከተው ግልጽ የሚያደርገው፤ በሥጋው ወራት ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ የተላከበት ተልዕኮ 
(mission) ለአይሁዶች ብቻ እንጂ ለአሕዛብ እዳልሆነ የሚያሳይ ነው። ማለትም በሥጋ ኢየሱስ መጥቶ አዲሱን ኪዳን እንዲመሠረት የተላከው ለአይሁዶች ነው። ማቴዎስ 10 ላይ ብንመለከት ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱን ሲልካቸው ወደ አይሁዶች ብቻ ነበር የላካቸው። ምክንያቱም ኢየሱስ በቅድሚያ ሕግን መፈጸምና በሕግ ያለነቀፋ ሆኖ መገኘት ነበረበት። በኤርምያስ 31፡31 ላይ እንደተጻፈውም አዲሱ ኪዳን መደረግ ያለበት ከእስራኤል ቤት ጋር ነው።

አይሁዳውያን የእግዚአብሔር ልጅ ራሱ መጥቶ ነው ወንጌልን የሰበከላቸው፤ ወደ አሕዛብ ደግሞ እንደ ጳውሎስ ያሉ ሐዋርያት ናቸው የተላኩት። ኢየሱስ ራሱ ወደ አሕዛብ ሁሉ እየሄደና ዓለምን እየዞረ ወንጌልን እንዲሰብክ ይህ ተልዕኮ አልተሰጠውም ነበር።

ስለዚህ ኢየሱስ በዚህ ክፍል የሚናገረው እስከሚሰቀል ድረስ በሥጋው እንደ እግዚአብሔር መልእክተኛ የተላከው ለአሕዛብ ወንጌልን ለመስበክ ሳይሆን ለአይሁድ እንደሆነ ነው። ለምሳሌ ጳውሎስ የእርሱን አገልግሎትና የኬፋን 
(የጴጥሮስን) አገልግሎት ሲያወዳደር፤ እርሱ ለአሕዛብ ጴጥሮስ ደግም ለአይሁድ እንደተላኩ ይገልጻል።
ወደ ገላትያ ሰዎች
2፥7 ተመልሰው ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ፤
2፥8 ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና።
2፥9 ደግሞ የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤

ልክ እንደዚሁ የኢየሱስም የሥጋው ወራት አገልግሎት ለአይሁድ ብቻ የተወሰነ ነበር።

የጠፉት በጎች ሲል ደግሞ ስለ አንድ ነገድ ወዘተ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ርቀው ስላሉ ኃጢአተኛ እስራኤላውያን እንደሚናገር የሚያሳዩ ክፍሎችን መመልከት ይረዳል።
የሉቃስ ወንጌል 5
30 ፈሪሳውያንና ጻፎቻቸውም በደቀ መዛሙርቱ ላይ። ስለ ምን ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ትበላላችሁ ትጠጡማላችሁ
? ብለው አንጐራጐሩ።
31 ኢየሱስም መልሶ፦ ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤
32 ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው።

በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 15 ያለውንም የጠፋውን ልጅ ታሪክ ስንመለከት፤ ሁለቱ ልጆች አንደኛው በቤት ያለው ሁለተኛው ደግሞ የጠፋው ልጅ ታሪክ የሚያወራው ስለ ነገዶች ሳይሆን በኃጢአት ስለወደቀና ከአባቱ ርቆ በኃጢአት ከጋለሞቶች ጋር ገንዘቡን ስለበተነ ኃጢአተኛ ልጅ ነው።

ስለዚህ ኢየሱስ ከእስራኤል ስለ ጠፉት ማለትም ከእግዚአብሔር ርቀው ኃጢአተኛ የሚባሉትን ሊፈልግ እንደመጣ ነው እንጂ የሚናገረው የሆነ የእስራኤል ነገድን ሊፈልግ አይደለም። በወንጌላቱ የተጻፉትን አገልግሎቱንም ስንመለከት ኢየሱስ ጋለሞታዎችን፤ ቀራጮችን፤ ኃጢአተኞችን ወዘተ ሲፈልግና እነርሱን ሲያገለግል ነው የምናየው
ወንድማቹ ሸዋፈራው አለነ
የጌታ ሰላም ከሁላችንም ጋር ይሁን

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ