ጌታ ኢየሱስን ማወቅ
የዘለአለም ህይወት ነው
ወዳጄ ሆይ መጽሐፍ ቅዱስን
ማንበብህን እወድልሀለው ግን አንድ የምመክርህ ምክር አለኝ ከማንበብህ አስቀድሞ የዘመናት ባለቤት ወደሆነው ወደእግዚአብሄር የቅዱስ
ቃሉን ሚስጥር ይገልጥልህ ዘንድ ፀሎትን አድርስ መንፈስ ቅዱስን ይልክልሀል አንተም በቃሉ ትፅናናለህ እረፍትን ታገኛለህ የኢሱስን
ማንነት ትረዳለህ እንደማንነቱ ታምነዋለህ እንደቃሉም ትኖራለህ መንግስቱንም ያወርስሀል፡፡ከእስማኤላውያን እና ከመናፍቃን ዘንድ ትጠነቀቅ
ዘንድ እመክርሀለው ምክንያቱም እነሱ መፅሀፍ ቅዱስን እንደማንኛውም ልቦለድ ተመልክተው ስለሚያነቡ በቃሉ ሲሰናከሉ እና ሲያሰናክሉ
እመለከታለው፡፡አንተ በቃሉ ትሰናከል ዘንድ አይገባም ምክንያቱም በጥምቀት የተቀበልከው ቅዱሱ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደእውነት እና
ኢየሱስን ወደማወቅ ያደርስሀል፡፡ወንጌልን ስታነብ ኢየሱስ በድንግልና ተወለደ ይልሀል አምላክ እንዴት ይወለዳል እንዳትል ሁሉን ቻይ
እንደሆነ ይወለድም ዘንድ የሚከለክለው እንደሌለ በልብህ እመን፤ወንጌል ኢየሱስ ተራበ በዲያብሎስ ተፈተነ ይልሀል እንዴ አምላክ እንዴት
ይራባል በዲያብሎስስ እንዴት ይፈተናል ብለህ እንዳትጠራጠር ምክንያቱም እሱ ፍጹም ሰው ሁኖ ከሀጢያት በቀር በሀሪህን በሀሪ አድርጎ
ወደዚህ ምድር እንደመጣ አስተውል ፤ወደ አባቱ ወደአብ ሲፀልይ ተመልክተህ አምላኬ አምላኬ ብሎ ሲጣራ አይተህ እንዴ እንዴት አምላክ
ሊሆን ይችላል እንዴት አምላክ ይጸልያል እንዴትስ አምላኬ ብሎ ሊጣራ ይችላል ብለህ ባምላክነቱ ላይ ያለህ እምነት ለሰከንድ እንኳን
እንዳይሸረሸር ምክንያቱም ቀድሞ እንደነገርኩህ የሚፀልይ ስጋን አምላኬ የሚል የሰው ባህሪን ባህሪው አድርጎ ተዋህዷል፤በሌላም ቦታ
ኢየሱስ ደከመው ሲል ታነብ ይሆናል ያንተን ደካማስጋ መዋሀዱን አትዘንጋ፤ስለመጨረሻው ዘመን ካባት ብቻ በቀር ልጅም ቢሆን አያውቅም
ሲል ትሰማው ይሆናል ነገር ግን አምላክ ሁኖ እንዴት ስለመጨረሻው ዘመን ዐያውቅም ብለህ በአምላክነቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳይኖርህ ምክንያቱም
ስለዘመኑ ፍፃሜ ስለሚያውቅ ምልክቶቹን ዘርዝሮ እንደነገረህ አስተውል ለምን አላውቅም አለ ብትለኝ አላዋቂ ስጋን እንደለበሰ ለማጠየቅ
ነው እልሀለው አንድም ሰው ልጆች እንደማያውቁ ለማሳወቅ ነው አንድም በግብር እንደማያውቃት ሲናገር ነው/ማለትም ፈራጅ ቃል እሱ
ነው በሚፈርድበት ጊዜ በግብር ቀኒቷን ያውቃል፤ሲበላ እና ሲጠጣ ትመለከተዋለህ እንዴት ብሎ አምላክ ይበላል እንዴትስ ይጠጣል ብለህ
እንዳትጠይቅ ምክንያቱም አምላክ ሰው መሆኑን አስታውስ ፤እንዴት ከራሤ አንዳች ማድረግ አይቻለኝም ብሎ ይናገራል ብለህ አምላክነቱን
እንዳትጠራጠር ሁሉን ማድረግ የማይችለውን የኛን ስጋን መዋሀዱን ታውቃለህና፤እንዴት አምላክ መከራ ይቀበላል እንዴትስ ይሞታል ብለህ
እንዳትጠይቅ ልብ በል የሚሞት መከራ የሚቀበል ስጋችንን ባህሪያችንን ከእመቤታችን ባህሪው አድርጓልና፡፡ አሁንም ወዳጄ ደግሜ እላለሁ
በቃሉ እንዳትሰናከል ተጠንቀቅ ራብ ያየኸው አምስት ሺ ህዝብ መመገቡን አትዘንጋ፤ከራሴ አንዳች ማድረግ አይቻለኝም ያለው ባህር እና
ነፋሳትን ሲገስፅ ብዙ በሰው ዘንድ የማይቻሉ ታምራቶችን ማድረጉን ተመልከት፤ሞቶ እና መከራ ተቀብሎ ያየኸው ትንሳኤአችን በኩር ሆኖ
ከሙታን ሲነሳ መከራችንን በመከራው ሲያስወግድ ተመልከት፤ሲበላ ሲጠጣ ያየኸው አርባ ቀን እና ለሊት መጾሙን አስታውስ፤ሲፀልይ እና
አምላኬ አምላኬ እያለ ሲጣራ ካየኸው አምላክ እንደሆነ ሰዎች ሲመሰክሩለት ፀሎት ተቀብሎ ህዝቡን ሲፈውስ እንደነበረ አስታውስ…………………………………………………ስለዚህም
ወዳጄ ከላይ የዘረዘርኩልህን አምላክ ሰው ሰው አምላክ የሆነበትን ድንቅ የሆነውን የተዋህዶ ምስጢር ለመመራመር አትሞክር ኢየሱስ
ፍጹም ሰው ፍፁም አምላክ ሁኖ በተዋህዶ የተገለጠ ድንቅ የአብ ልጅ የማርያም ልጅ አልፋ እና ኦሜጋ ያለ የነበረ ተመልሶ ሚመጣ ጌታ
አዳኝ ንጉስ ሰው የሆነ አምላክ አንድ አካል አንድ በሀሪ በተዋህዶ ብለህ አምልከህ ትዛዙን ህጉን ከፈፀምክ አትጠራጠር የዘላለም
ህይወትን ትወርሳለህ ማራናታ
የአብ ፀጋ የወልድ ቸርነት
የመንፈስ ቅዱስ ህብረት የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን አሜን
የክርስቶስ ሰላም ከሁላችንም
ጋር ይሁን አሜን
ወንድምህ ደቀመዝሙር
ሸዋፈራው አለነ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ