የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሲባል እና እኛ ስንባል
አንድ ነው?
መቼም በዚህ በፌስ ቡክ የማናየው የማንሰማው የማናነበው
የመናፍቃን ጉድ የለም ፡፡ ባለፈው ታስታውሱ እንደሆነ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ጌታ አዳኝ አምላክ መሆኑን ፖስት አድርጌ ነበር
፡፡ፖስት ካደረኩት ጽሑፍ ውስጥ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ሲባል አምላክ /እግዚአብሔር/ነው ማለት ነው የሚል ቃል አለ ኦርቶዶክስ
መልስ አላት በሚለው ግሩፕ ውስጥ አንድ መናፍቅ ወዳጄ/ፕሮቴስታንት ነው/ ‹‹ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ይህም ማለት እግዚአብሔር
ነው ማለት ነው ብለሀል እኛም የእግዚአብሔር ልጅ ተብለን ስለተጠራን እግዚአብሔር ነን ማለት ነው›› ብሎ ኮሜንት ሰጠኝ በወቅቱ
እኔም መልስ የመለስኩለት ቢሆንም መናፍቃን ምን ያክል ባለማወቅ ወይም ላለማወቅ በማሰብ ሲጠፉ እና ሰው ሲያጠፉ እያየሁ ዝም ማለት
ስላቃተኝ እስቲ እኛ የእግዚአብሔር ልጅ ስንባል እና ጌታ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ መፅሐፍ ቅዱስን
መሰረት አድርገን እንማማራለን፡፡
በመሰረቱ እነሱ/መናፍቃን/ የእግዚአብሔር ልጆች
እንዳልሆኑ ልታውቁልኝ እወዳለው የእግዚአብሔር ፍጡሮች እንጂ ልጆች አይደሉም የእግዚአብሔር ልጆች የሚባሉት የኢየሱስን አዳኝነት
ጌትነት አምላክነት እውነተኛ ማንነት ተረድተው እና አምነው ህጉና/ወንጌል ህግ/ ትእዛዙን የሚያከብሩ ናቸው፡፡
1.ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ሲባል፡-
በወንጌልም ሆነ በተለያዩ የሀዲስ ኪዳን የመልእክት
ክፍሎች ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ተጠቅሶ ይገኛል እንደውም ማንኛውም ክርስቲያን እግዚአብሔር
ልጅ መሆኑን ማመን መቀበል እንዳለበት አጽንኦት ተሰጥቷል ፡፡ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቂሳርያ ሀዋርያቱን ሰብስቦ ሰዎች ማን እንደሚሉት
በጠየቃቸው ጊዜ አንዳንዶች ኤልያስ ከነብያት አንዱ እንደሆነ እንደሚናገሩ ሲነግሩት እናንተ ማን እንደሆንኩ ትላላችሁ ብሎ ቢጠይቃቸው
ክርስቶስ የህያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ቅዱስ ጴጥሮስ ተናግሯል ጌታችንም ቅዱስ ጴጥሮስን አመስግኖ ስጋና ደም እንዳልገለጠለት
የሰማዩ አባቱ እንደገለጠለት በመናገር በዚህ በቅዱስ ጴጥሮስ ንግግር ቤተክርስቲያኑን እንደሚመሰርት ጌታ ተናግሯል ክርስቶስ የእግዚአብሔር
ልጅ ነው የሚለው የቅዱስ ጴጥሮስ ንግግር የቤተክርስጢያን መሰረት ነው የጌታን ማንነት የሚገልጽ እምነታችን መሰረት ነው፡፡ኢየሱስ
የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ የማያምን እንዲሁም ብሎ የማይመሰክር ሰው ክርስቲያን ተብሎ ሊጠራ አይችልም ምክንያቱም የክርስትና መሰረት
ይህ ስለሆነ ፡፡
‹‹ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ
መዛሙርቱን። ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ።
|
እርሱም፦ አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥
ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት።
|
እርሱም፦ እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?
አላቸው።
|
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥
በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።
|
እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ
ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።
|
የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር
የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።››ማቴ 16፡13-19
|
ቅዱስ ገብርኤልም እመቤታችንን ለማብሰር በተላከ
ጊዜ ከሷየሚለደው ቅዱሱ የእግዚአብሄር ልጅ እንደሚባል ነግሯታል እሷም
ይህንን በእምነት ተቀብላ ስግው ቃል/ሰው የሆነ አምላክ/ እግዚአብሄርን በስጋ ወልዳዋለች ስለዚህም ወላዲተ አምላክ ብለን እንጠራታለን፡፡
የሉቃስ ወንጌል 1፡35
|
‹‹መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ
ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።››
|
በተለያየም ቦታ አጋንንት እኳን ሳይቀሩ የእግዚአብሔር
ልጅ እንደሆነ መስክረዋል፡፡ ማቴ 8፡29 አይሁድም የእምነታችን መሰረት የሆነውን የእግዚአብሔር ልጅነቱን አልተቀበሉም ነበር፡፡ማቴ
26፡63 ይዘብቱበትም ነበር ማቴ 27፡43 ፡፡ቅዱስ ማርቆስም ወንጌሉን ሲጀምር እግዚአብሔር ልጅነቱን መስክሮ ነው ማር1፡1 ፡፡በተለያየ
የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ክፍል ውስጥ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ተጠቅሷል ይህንንም እናመን ዘንድ ወንጌል እንደተፃፈ ይነግረናል
ዮሐ 1፡34 ፤1፡50 ፤6፡69 ፤ 10፡36 ፤11፡4 ፤11፡27 ፤ 19፡7 ፤ 20፡31፡፡ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ይህንን አምኖ
እንደተጠመቀ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ሐዋ 8፡37፡፡ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱም ኢሱስ የእግዚአብሄር ልጅ እንደሆነ ተናግሯል‹‹ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ
ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል።››1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፡15፡፡ እንግዲህ
ከላይ እንደተመለከትነው መጽሀፍቅዱስ አፅንኦት ሰጥቶ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በእግዚአብሔር ልጅነቱም ማመን
እንዳለብን ይናገራል ለመሆኑ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ሲባል ምን
ማለትነው ?
ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ሲባል መፅሐፍ
ቅዱስ እንደሚነግረን እግዚአብሔር ነው ማለት ነው ፡፡እኛ የሰው ልጆች
ሰዎች እንደምንባል ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስም እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል ፡፡ ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው ሲባል አብን
በመልክ የሚመስለው በባህሪ የሚስተካከለው ማለታችን ነው ዮሐ 1፡1-3 ፤ ዮሐ 10 ፡30 ፤ዮሐ 14፡8-10 ‹‹እኔና አብ አንድ
ነን እኔን ያየ አብን አይቷል››፡፡ ልጅነቱም የባህሪ ልጅነት ነው ማለትም ከማንም ያልተቀበለው ማንም የማይወስድበት ዘላለማዊ ልጅነት
ነው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ ልጅ እንደሆነ
ከአብ ጋር አንድ እንደሆነ እና አብ የሚያደርገውን ሁሉ እንደሚያደርግ ለአይሁድ ሲነግራቸው ድንጋይ አንስተው ሊወግሩት በማሰባቸው
ጌታችን ስለምን ትወግሩኛላቻሁ ባላቸው ጊዜ ስለመልካም ስራህ አንወግርህም ስለስድብህ ነው ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለማድረግህ ነው ማለታቸው በወንጌል ተመዝግቧል
እንግዲህ አይሁድ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ማለቱ አምላክ ነኝ ማለቱ እንደሆነ ገብቷቸዋል ማለት ነው ዮሐ 10፡25-38 ፡፡ ከዚህ ጥቅስ እንደምንረዳው ጌታችን ራሱን የእግዚአብሔር
ልጅ ብሎ መጥራቱ አምላክ ነኝ ማለቱ እንደሆነ ነው/ ሙሉውን የአይሁድ እና የጌታን ንግግር አንብቡት/፡፡በሌላም ቦታ አይሁድ የእግዚአብሔር
ልጅ ነኝ ብሎ ራሱን መጥራቱን ተቃውመው ሊገሉት እንደነበር የእግዚአብሄር ልጅ ነኝ ማለቱ ደግሞ እግዚአብሔር ነኝ ማለቱ እንደሆነ
ተረድተውት ሊገሉት እንደሚፈልጉ ተገልጧል ‹‹እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር
ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር።››ዮሐ 5፡18
ስናጠቃልለው ኢየሱስ እግዚአብሔር ልጅ ተብሎ መጠራቱ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተመለከትነው አምላክ/እግዚአብሔር መሆኑን የሚገልጥልን ልጅነቱም ከማንም ያልተቀበለው ባህሪ ልጅነት እንደሆነ
እግዚአብሄርንም የሚስተካከልበት ልጅነት በመልክ ሚመስልበት ልጅነት እንደሆነ ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡
2.እኛ እግዚአብሔር ልጅ ስንባል፡-
እንግዲህ ከላይ እንዳነው ኢየሱስ በተለያየ የመፅሀፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ የእግዚአብሔር
ልጅ ተብሎ እንደተጠራ እግዚአብሔር ልጅ መባሉ ባህሪልጅነት እንደሆነ ተመልክተናል ፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ ብቻም ሳይሆን
እውነተኛ አማኞችም እግዚአብሄር ልጆች ተብለው ተጠርተዋል/ተጠርተናል/ ፡፡ታድያ የእግዚአብሔር ልጅ መባላችን እንደ ኢየሱስ ልጅነት
ካነው በጣም ተሳስተናል ክህደት ውስጥም እንገባለን እኛ እውነተና አማኞች የእግዚአብሄር ልጆች ተብለን ስንጠራ የባህሪ ልጅነት ሳይሆን
የፀጋ ልጅነት እንዳለን የሚያመለክት ነው ፡፡ፀጋ ማለት ያለዋጋ የሚገኝ ነፃ ስጦታ ማለት እንደሆነ እናውቃለን ፡፡
የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ልጅነት ያገኘው በስጦታ
ነው ያገኘበት ምክንያትም እንደሚከተለው እናያለን፡-
1.ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በመቀበላችን/በማመናችን/
የዮሐንስ ወንጌል
|
||
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች
ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤
|
||
የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልን ስንመለከት
የሰው ልጆች የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው የተጠሩት በስጦታ ነው ያም ስጦታ የተገኘው ጌታን በማመናችን ነው ይህም የፀጋ ልጅነት
ተብሎ ይጠራል፡፡
2.በመጠመቃችን
የዮሐንስ
ወንጌል 3
2 መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር
ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር
ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው።
|
ከጌታችን እና ከኒቆዲሞስ ንግግር እንደምንረዳው
ሰው በውሀ እና በመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ እንደማይጠራ መንግስቱንም እንደማይወርስ /ምክንያቱም የአባቱን
ንብረት የሚወርሰው ልጅ ስለሆነ/ ነው፡፡ ሁለተኛው ልጅነትን ያገኘነው በጥምቀት ነው ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡
ስናጠቃልለው ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መባሉ
የባህሪ ልጅ እንደሆነ ልጅነቱንም ከማንም ያልተቀበለው መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡እኛ ትክክለኛ አማኞች የእግዚአብሔር ልጅ ስንባል
በማመናችን ያገኘነው ስጦታ እንደሆነ እና ከኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት የተለየ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
የእግዚአብሔር ሰላም ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን
የአብ ጸጋ የወልድ ቸርነት የመንፈስ ቅዱስ አንድነት
የእመቤታችን አማላጅነት ከሁላችንም ጋር ይሁን
ወንድማችሁ ደቀመዝሙር ሸዋፈራው አለነ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ