አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ›› (ማቴ 27፡46)/ይድረስ ለአህዛብ እና አርዮሳውን/
‹‹ልጁ እራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል›› 1ኛ ቆሮ 15፡22 ምን ማለት ነው
በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ውድ እህትና ወንድሞቼ እንደምን አላቹልኝ እንደእግዚአብሔር ፈቃድ ዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እውነተኛ ትርጉም እናያለን ብዙ ጊዜ እስላሞች ራሳቸውን የይሖዋ ምስሮች በማለት የሚጠሩ አርዮሳውያን እና መናፍቃን ፕሮቴስታንቶች እና ያናገርኳቸው አንዳንድ ተሀድሶዎች ይህንን ጥቅስ በመያዝ ወልድ ሁሉን እንዲገዛ ስልጣንን የሰጠው አብ ነው ነገር ግን ወልድ ሁሉን ላስገዛለት ለአብ ይገዛል ስለዚህ ወልድ ከአብ ያነሰ ስልጣን ነው ያለው ይላሉ፡፡አህዛብ እና አርዮሳውያን ይህንን ቢሉም አይደንቀኝም ነገር ግን የኢየሱስን አምላክነት እናምናለን ሥላሴም እንታመናለን ብለው የሚናገሩ ፕሮቴስታንቶች ይህንን ማለታቸው በጣም የሚያሳዝን እና በአንደበት አምላክነቱን እናምናለን ቢሉም በተግባር እንደካዱት የሚያሳይ ነው፡፡
ገፀ ንባቡን በማስተዋል ካነበብነው ቅዱስ ጳውሎስ እየተናገረ የመጣው ስለትንሳኤ ሙታን እና ክርስቶስ ሞትን ድል ስለማድረጉ ብሎም ሞት በሁሉም ላይ ስላለመሰልጠኑ ኃይሉንም ስለመሻሩ ነው እስኪ ከቁጥር 20 ጀምረን እንመልከተው ‹‹አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነስቷል ሞት በሰው በኩል ስለመታ ትንሳዔ ሙታን በሰው በኩል ሆኗል ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁም በክርስቶስ ህያዋን ይሆናሉና ነገር ግንእያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል ክርስቶስ እንደበኩራት ነው በኋላም በመምጣቱ ለክረስቶስ የሆኑት ናቸው በኋላም መንግስቱን ለአባቱ ለእግዚአብሔር አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ስልጣንንም በሻረ ጊዜ ፍፃሜ ይሆናል ››አለቅነትንም ስልጣንንም በሻረ ጊዜ ፍፃሜ ይሆናል የሚለው የአለም ፍፃሜ የሚሆነው የዚህ አለም ገዢዎች እና አለቆች ስልጣናትን ኃይላትን ስልጣናቸው ተሽሮ መሆኑን ለማስረዳት ነው ምክንያቱም በሌላም ቦታ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል ‹‹መጋደላችን ከስጋና ከደም ጋር አይደለምና ከአለቆችና ከስልጣናት ከዚህም ከጨለማ አለም ገዥዎች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ባሉ ከክፋት መንፈሳዊ ሰራዊት ጋር ነው እንጂ››ኤፌ 6፡12 ቀጥሎ ደግሞ ከቁጥር 25-27እንዲህ ይላል ‹‹ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግስ ይገባዋልና የኃለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቷልና ነገር ግን ሁሉ ተገዝቷል ሲባል ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው ››
‹‹ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግስ ይገባዋልና ››የተባለው ለወልድ ነው ጠላቶች የተባሉትም ሞትና ዲያብሎስ ናቸው፡፡ዘፍ 3፡15 እንዲ ተብሏል ‹‹በአንተ እና በሴቲቱ በዘርና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለው ››በምፅአት ቀን የሞትና የዲያብሎስ ስልጣን ያከትማል ‹‹ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግስ ይገባዋል ››ሲል ከገዛ በኋላ እንደምድራዊ ሹም ሥልጣኑን አስረክቦ ይወርዳል ለማለት ሳይሆን ለዘለአለም ንጉስ ሆኖ ይኖራል ማለት ነው እዚህ ላይ የገባችው ‹‹እስከ›› ፍፃሜ የለሽ ወይም ዘላለማዊ‹‹እስከ›› ነች ለምሳሌ ‹‹የሳኦል ልጅ ሜልኮል እስከሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አላወለደችም ››2ሳሙ6፡23ይህ ማለት ሜልኮል ከሞተች በኋላ ወልዳለች ለማለት ሳይሆን ለዘለአለም ሳትወልድ ቀረች ማለት ነው ዘፍ 8፡6‹‹ቁራውም ውሀው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይል ነበር ››ይላል እዚህ ላይም ቁራው ውሀው ከጎደለ በኋላ ተመለሰ ለማለት ሳይሆን እስከመጨረሻው ሳይመለስ ቀረ ለማለት ነው ኖህ ቁራው ሳይመለስ ስለቀረ ነው እርግብን የላካት፡፡ አንድም ስልጣኑን ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ የተባለው ጌታ በወንጌሉ ‹‹እረኛው አንድ መንጋውም አንድ››ዮሐ 10፡16 እንዳለ በመጨረሻው ዘመን የክርስቶስ መንግስት በስላሴ መንግስት ይጠቃለላል ማለትም ክርስቶስ ብቻ ይገዛ የነበረው የምድራዊ መንግስት/ሞቶ ስላዳነ ያዳናቸውን ሰዎች እየገዛ ያለው ክርስቶስ ስለሆነ/ያ የብቻው መንግስት በክርስቶስ ተጠቅልሎ የስላሴ መንግስት ይሆናል ማለቱ ነው ፡፡ክርስቶስ መንግስቱን ይተዋል ማለት ግን አላዋቂነት ነው ምክንያቱም በተለያየ ቦታ ለዘለአለም እንደሚገዛ ነው የተፃፈው ሉቃ 1፡33፤ዕብ1፡8
ቀጥሎ ደግሞ ‹‹ሁሉ ተገዝቷል ሲል ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው ›› ሁሉ የተባለው ከአዳም ጀምሮ ያለው የሰው ዘር ነው ሞት የሰው ዘርን በሙሉ ከትንሽ እስከትልቅ ፃድቃን እና ሀጥእ ሳይል ሁሉን ገዝቶ በሁሉም ላይ ሰልጥኖ ይኖር ነበር ነገር ግን ሞት ሁሉን ገዛ ቢባልም‹‹ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው››ሁሉን ያስገዛለት የተባለው እግዚአብሔር ነው፡፡ሐዋርያው ይቀጥልና ቁጥር 28 ላይ ‹‹ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል››ይህም ማለት የእግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁ ወልድ ሁሉን ላስገዛለት ለሞት እሱ ራሱ በስጋው ይገዛለታል ማለት ነው፡፡ሞት ወልድን ሳይቀር በስጋው ይገዛዋል ነው ምክንያቱም እንዲህ ተብሏል ‹‹የባርያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሁኖ ራሱን ባዶ አደረገ……ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳን የታዘዘ ሆነ››ፌል2፡7-8ወልድ ‹‹ለሞት ተገዛ ››ስንል በፈቃዱ ነው በእለተ አርብ በቀራንዮ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ስጋው በገዛ ስልጣኑ መለየቱን ለማስረዳት ነው፡፡አስቀድሞ ጌታ እንዲህ ብሏል ‹፣ነፍሴን ደግሞ አነሳት ዘንድ አኖራታለውና›› ……እኔ በፍቃዴ አኖራታለው እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም ላኖራት ስልጣን አለኝ ላነሳት ስልጣን አለኝ፡፡ዮሐ10፡17-18 ስንጠቀልለው ልጁ ራሱ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል ማለት ለአብ ይገዛል ማለት ሳይሆን ከላይ እንዳየነው ሁሉን ላስገዛለት ሞት በፈቃዱ ይገዛል ይህም ተፈፅሟል የመፅሐፍ ልማድ የተደረገውን ገና እንደሚደረግ ያልተደረገውን እንደተደረገ አድርጎ ማውራት ልማድ ነው፡፡
ይቆየን
ወንድማቹ ሸዋፈራው አለነ
ወስብሀት ለእግዚአብሔር
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ