“ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በህይወት ይኖራል”።ዕብ 7:-25
ይህንንም ጥቅስ በመያዝ ብዙ ጊዜ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ጌታ ኢየሱስ ይኸው ዛሬም ስለ እኛ ኃጢአት እንደሚያማልድ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ጻድቃን ፣ ሰማዕታት መላእክትና ድንግል ማርያምን አማልዱኝ ማለት አያስፈልግም ይላሉ። በቅድሚያ ቃሉን በደንብ ለመረዳት ገጸንባቡን ከላይ ከፍ ብለን በደንብ እንመልከት።
እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው። እርሱ ግን ለዘለዓለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው። ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በህይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። ዕብ 7:-23-25
እዚህ ላይ ሐዋርያው ሁለት መሠረታዊ ነጥቦችን ያሳየናል።
፩ኛው የሌዊ እና የአሮን ልጆች ካህናት እነርሱ ሟቾች እንደሆኑና ሕያዋን እንዳልሆኑ ሥልጣናቸውም የሚለወጥ በመሆኑ በእነርሱ አገልግሎት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ፍጹም መቅረብ እንዳልተቻለ ያሳያል።
፪ኛው ነጥብ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘለዓለማዊ በሞት የማያልፍ ክህነቱም የማይለወጥ በመሆኑ አንድ ጊዜ ያቀረበው መስዋዕት ዘለዓለማዊና የማይለወጥ ስለሆነ ስንታረቅበት የምንኖር መሆኑን ያሰየናል።
አንባቢ አስተው ልገደል አትግባ!!! ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከላይ ጀምሮ እየገለጸ የመጣው የኦሪት ካህናት አገልግሎታቸው ምን እንደሚመስል ነው። የኦሪት ካህናት ከነገድ ተመርጠው ከሌዊ ወገንይለያሉ ሊቀ ካህንነት ደግሞ የአሮን ልጆች ይሾማሉ። ታዲያ ካህናቱ ስለህዝቡ ኃጢአት የበግ እና የጊደር መስዋዕት በእግዚአብሔር ፊት የደኅንነት መስዋዕት እያሉ በየእለቱ ያቃጥላሉ፤ ነገር ግን ይህን አገልግሎት ለዘመናት እየፈጸሙ ቢኖሩም ፍጹም የሆነ የነፍስ ድኅነት ሊያመጡ አልቻሉም። እንኳን ሕዝቡን ራሳቸውን እንኳ በክህነት እገልግሎታቸው ማዳን አልቻሉም ሊቀ ካህናቱ በተለይ ስለሕዝቡና ስለ ራሱ ኃጢአት በዓመት አንድ ጊዜ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ በግ ይሰዋል ይህ የስርየት መስዋዕት በየዓመቱ ይሰዋል ሆኖም ግን ጊዜያዊ የሥጋ መከራና መቅሰፍቶችን ከማራቅ ባለፈ የነፍስ ድህነትና የዘለዓለም ህይወትን ማስገኘት አልቻለም ካህናቱ እንዲህ እያገለገሉም በሞት ይነጠቃሉ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ ነበረባቸው። ለምን ቢባል በአዳምና በሄዋን ምክንያት በዘር የሚተላለፈው ኃጢአት ወይም የውርስ በደል እነርሱም ላይ ስለነበረባቸው “ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው”፤ የተባሉት የኦሪት ካህናት ናቸው።
“እርሱ ግን ለዘለዓለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም የባህርይ አምላክ ስለሆነ ለዘመኑ ጥንት ወይም ፍጻሜ የለውም። ዓለም ሳይፈጠር ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ህይወቱ ከመንፈስቅዱስ ጋር በቃልነት ህልው ሆኖ ይኖር ነበር። ዓለምንም አሳልፎ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ይኖራል። ለዚህ ነው ዕብ ፲፫፦፰ ላይ “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘለዓለም ያው ነው” የተባለው፤ ክህነቱም ከሰው የተገኘ ሹመት ሳይሆን የባህርይ ገንዘቡ ስለሆነ ዘላለማዊ ካህን ነው፤ “አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ”፤ ተብሏል። ዕብ ፯፦፲፯
“ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በህይወት ይኖራል”
ስለ እነርሱ የተባሉት እንዳይኖሩ ሞት የከለከላቸው ካህናት ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ አርብ የማስታረቅ አገልግሎት የፈጸመው ወደፊት ስለሚነሳው ትውልድ ወይም በወቅቱ ስለነበሩት የአዳም ልጆች ብቻ ሳይሆን ጌታ ከመወለዱ በፊት ለነበሩትም ጭምር ነው። በመስቀል ላይ ራሱ መስዋዕት፣ ራሱ መስዋዕት ሰዊ ፣ ራሱ መስዋዕት ተቀባይ ሆኖ የድህነትን አገልግሎት ሲፈጽም በጊዜና በቦታ ሳይገድብ ዓለምን በሞላ እና የአዳም ልጆችን በሙሉ ነው ያዳነው ስለዚህ “ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በህይወት ይኖራል” የተባለው ከጌታ በፊት ለነበሩት ካህናት ነው። ሆኖም ግን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋው ወራቱ የፈጸመው የማማለድ ተግባር አንዴ የተፈጸመና ነገር ግን ሕያው ሆኖ ለዘላለምየሚኖር ነው። እግዚአብሔር ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት ብሎ አንዴ የተናገራት ቃል ሕያው ሆና ለዘለዓለም እንደምትሰራ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ ወራት በምድር ላይ የፈጸማት የማስታረቅ አገልግሎት ሕያው ሆና ለዘለዓለም ዓለምን ከእርግማንና ከውርስ ኃጢአት ስታድን ትኖራለች ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ላይ ወረድ ይልና “እርሱም \ክርስቶስ\ እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለራሱ ኃጢአት በኋላም ስለሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መስዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጓልና”። ይላል ዕብ ፯፦፳፯ ምናልባት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ዛሬም ኢየሱስ እየወደቀ እየተነሳ ይማልድልናል ካሉ ሁለት ስህተቶችን እየፈጸሙ ነው።
፩፦ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ የፈጸመው የማዳን ሥራ ያልተሟላና ያላለቀ (incomplete) ነው እንደ ማለት ይቆጠራል፤
፪፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም እራሱን ዕለት ዕለት መስዋዕት እያደረገ ያቀርባል፤ ዕለት ዕለት ያነባል ፤ ይጮሃል፣ ይጸልያል እንደ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ዘላለማዊ ክህነቱን ምድራዊ ብቻ እንደ ማድረግ ይሆናል።
ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ሰውና እግዚአብሔርን ለማስታረቅ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ሆኖ ማለትም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ሆኖ የማስታረቅ አገልግሎትን ሲፈጽም የመስቀል መከራን ተቀብሏል ፣ አልቅሷል ፣ ማልዷል ይህ አንድ ጊዜ የፈጸማት የማስታረቅ አገልግሎት ዘላለማዊ እንደሆነች አሁንም መጽሐፍ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል።
“ሊቀ ካህናትም በየአመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ ራሱን ብዙ ጊዜሊያቀርብ አልገባም!!!”።
እናስተውል!!! ራሱን ያለው ክርስቶስን ነው።
እናስተውል!!! ራሱን ያለው ክርስቶስን ነው።
ቀጥሎ እንዲህ ይላል “እንዲህ ቢሆንስ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራስን በመሰዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጧል። ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደተመደበባቸው እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል”። ዕብ ፯፦፳፭-፳፯
በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስ በዕብ ፭፦፯፡፲ ላይ "በሥጋው ወራት ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ ካለ በኋላ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸውም" ይላል ። እንግዲህ ጌታ በሥጋው ወራት የፈጸማት ምልጃ ለሚታዘዙለት ሁሉ ማለትም ያመነ የተጠመቀ ይድናል ብሎ ያዘዘውን ትዕዛዝ ለሚፈጽሙ ፣ ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘለዓለም ህይወት አለው ላለው መመሪያ ተገዥ ለሆኑ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህች ናት ላለው ሕግ ለሚታዘዙለት ሁሉ ለዘላለም መዳን ምክንያት ሆኖላቸዋል። ማር ፲፮፦፲፮ ፣ ዮሐ ፮፦፶፫ ፣ ፲፭፦፲፪
የማንታዘዝለት እና አመጸኞች ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ህግጋቱን የምንሸራርፍ ደካሞች ከሆንን ግን ንስሐ እየገባን ፣ ስለ ኃጢአታችን ፣ እያለቅስን በደላችንን እያስታወስን የክርስቶስን ውለታ በመርሳታችን ወዮልኝ! ወዮታ አለብኝ! እያልን ቅዱሳንን በጸሎታችሁ እርዱኝ አግዙኝ እያልን እንደገና ህይወት ወደ ሚሰጠን ጌታ መቅረብ እንችላለን።
ሌላው ስለ እነርሱ ሊያማልድ ዘወትር በህይወት ይኖራል ማለት እንደቀደሙት ካህናት ያይደለ የእርሱ ክህነት የማይለወጥ በመሆኑ አንድ ጊዜ ያቀረበው መስውዕትም ብዙዎችን ለማዳን ሕያው ሆኖ የሚኖር ዘላለማዊ መሆኑንና ዛሬ የምንሰዋው መሥዋዕት \ሥጋ ወደሙ\ ከዕለተ አርቡ ጋር አንድ ስለሆነ ዘወትር ሲያስታርቀን ይኖራል ማለት ነው። እንዲህ ተብሎ ተጽፏል ሊቀካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሟል እርሱ ግን ስለኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ተቀመጠ። ዕብ ፲፦፲፩
በተጨማሪም ሮሜ ፫፦፳፫ ላይ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነ ቤዛነት በኵል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ። ካለ በኋላ እርሱንም በእግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም ማስተስረያ አድርጎ አቆመው፤ ይላል።
ዕብ ፯፦፳፭ የመጨረሻው ዓረፍተ ነገር እንዲህ ይላል በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። ይህም ማለት ኢየሱስ የእግዚአብሔር አብ የባህርይ ልጅ እንደሆነና ስለኃጢአታቸው እንደ ሞተላቸው አምነው ወደ እግዚአብሔር የሚጡትን ያድናቸዋል። አንድም በእርሱ ትምህርት እና ተአምራት ተማርከው ከኃጢአት ከአምልኮ ባዕድ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል ማለት ነው።
ይችላል ያለበትም መርጦ መሄድ የእነርሱ ፋንታ መሆኑን ሲያስረዳ ነው። ታዲያ ይህን የቀና ትምህርት በማጣመም ሌሎችን ለመቃወም ሲባል ወደ ጥልቁ መወርወር ምን ይሆን???
ይችላል ያለበትም መርጦ መሄድ የእነርሱ ፋንታ መሆኑን ሲያስረዳ ነው። ታዲያ ይህን የቀና ትምህርት በማጣመም ሌሎችን ለመቃወም ሲባል ወደ ጥልቁ መወርወር ምን ይሆን???
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ