አፅናኙ ማነው?/ይድረስ ለመሀመዳውያን/
መቼም ብዙ ጊዜ በዚ በፌስ ቡክ የማናነበው የለም ሁሉም አማኙም መናፍቁም አህዛቡም የመፅሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ እኔ ነኝ ይህ ማለት ይህ ነው እያለ የራሱን ትርጉም መስጠት ተያይዞታል፡፡በዚህ ለምን አልሰለምኩም በሚለው ፔጅ ውስጥ አን ወዳጅ ሙስሊም አለኝ እሱም በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ የራሱን የሆነ ትርጉም አስቀምጧል እስቲ አብረን እንመልከተው፡-
<<@ኢየሱስ (አ.ሰ) በመፅሀፍ ቅዱስ ለነብያችን ሙሀመድ (ሰ.አ.ወ) መምጣት ብስራት (ትንቢት) ሲናገሩ፦ ገና የምነግራችሁ ብዙ አለኝ ። ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችሃል፤የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤የሚመጣውንም ይነግራችሃል። እሱ ያከብረኛል።ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችሃልና። ፼፼፼፼ እውነትም ነብያችን (ሰ.አ.ወ)ከራሳቸው ሳይሆን ከአላሀ (ሱ.ወ) የሚነገራቸውን ብቻ ይናገራሉ። እየሱስንም ያከብራል። ስለ እየሱስ አላሀ የነገረውን ሁሉ ተናግራል። አለምንም ወደቀጥተኛው የኢብራሂም መንገድ (ወደ ኢስላም) መርታል። አላሁ አክበር›› በመጀመሪያ አንድ ነገር ላስታውሳችሁ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመጨረሻው ዘመን ሲናገር ወንጌል ለአህዛብ ምስክር ይሆን ዘንድ በአለም ሁሉ ይሰበካል ያለው ቃል እየተፈፀመ መሆኑን አሁን ያለነው ፍፃሜ ዘመን ላይ እንዳለን ነው ማቴ 24፡14 ከላይ እንዳየነው ሙስሊሙ ወዳጃችን /የሌሎቹም ሙስሊሞች አመለካከት ነው /ጌታኢየሱስ አፅናኙ መንፈስ ይመጣል ያለው መሀመድን ነው ብሏል፡፡ እስቲ አንድ ነገር ልንገርህ ወዳጄ ይህንን የጌታን ቃል ለመሀመድ ሰጥተክ ከተናገርክ ሌላውንም የወንጌል ቃል ማመን እንዳለብህ ማወቅ አለብህ አንዱን ቃል ብቻ መዞ ማመን አይቻልም ጌታ ስለሀጥያታችን መሞቱን መሰቀሉን መነሳቱን ሰው መሆኑን አዳኝ ጌታ አምላክ መሆኑን ማመን አለብህ ምክንያቱም በወንጌል ተመዝግቦ ያለውን የጌታ ቃል ለመሀመድ እንደተነገረ በማመንህ የወንጌልን እውነተኛነት ተቀብለሀል ማለት ነው ይህንን ስል ትንቢቱ ለመሀመድ ተነገረ እያልኩኝ አይደለም፡፡ ትንቢቱ የተነገረው ይመጣል የተባለው አፅናኝ መሀመድ ነው ካላችሁ እነዚህን ጥያቄዎች መልሱ 1.ጌታ መንፈስ እንደሚመጣ ነው የተናገረው መሀመድ መንፈስ ነው እንዴ? ስጋና አጥንት የለውም? ሰውስ አይደለም እንዴ? ይህንን እንድትመልሱልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ጌታ ይመጣል ያለው አፅናኙ መንፈስ እንጂ ስጋና አጥንት ያለው ሰው ነው አላለም፡፡ 2.ለመሆኑ መሀመድ ኢየሱስን አክብሯል እንዴ? ምክንያቱም ኢየሱስ የያከብረኛል ስላለ 3.ኢየሱስ ከእኔ ወስዶ ይነግራችኋል ብሏል መሀመድ ከኢየሱስ ወስዶ እንደተናገረ ታምናላችሁ? በተረፈ የጥቅሱን ሀሳብ ፍሬ ነገር በዝርዝር ቀጥሎ እንመልከት፡- ‹ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ። ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ዮሐንስ 14.15-18፡፡ ‹ከእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል። ዮሐንስ 14.25-26፡፡ ‹ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ። ዮሐንስ 15.26-27፡፡ በሚገርም ሁኔታ ሙስሊሞች እነዚህን ጥቅሶች የሚያዩአቸው ስለ መሐመድ መምጣት ትንቢቶች እንደሆኑ አድርገው ነው፡፡ በእርግጥ ስለ አፅናኝ የተነገረባቸውን እነዚህን ሦስት ጥቅሶች በሙሉ ከጠቀሰ በኋላ፣ ሙላና መሐመድ አሊ የያዘው ‹ሁሉም እነዚህ የትንቢት ቃሎች ያለምንም መዛነፍ የሚናገሩት ነገር ከኢየሱስ በኋላ ስለሚመጣ ሌላ ነቢይ ነው›፡፡ የሚልን አቋም ነው፡፡ Maulana Muhammad Ali, Muhammad in the Bible, p. 27. ‹ኢየሱስ ወደ አባት ካልተመለሰ በስተቀር አፅናኙ አይመጣም› የሚለው ይህ ትንቢት ስለ መንፈስ ቅዱስ በፍፁም ሊናገር አይችልም በማለት ሙስሊሞች ይከራከራሉ፡፡ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ በራሱ በኢየሱስ ውስጥ ስለነበረ ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህም ኢየሱስ ይናገር የነበረው ስለ ሌላ ነቢይ መነሳት ወይንም መምጣት ነበረ፣ ስለዚህም (ለተወሰኑ ምክንያቶች) ተመራጭ ሊሆን የሚችለው ነቢይ መሐመድ ብቻ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት አባባል ደግሞ የዮሐንስ ወንጌልን ለሚያውቅ ሰው እጅግ አስገራሚ ነው የሚሆነው፡፡ በመጀመሪያ ሙስሊሞች ይህንን ትንቢት ወሰድን የሚሉት ከመጀመሪያው ጀምሮ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን እና ሁሉን ነገር የፈጠረ ነው ከሚለው መጽሐፍ ማለትም ከዮሐንስ 1.1-3 ላይ ነው፡፡ በዮሐንስ መጽሐፍ ኢየሱስ የተናገረው ከአብርሐም በፊት እርሱ እንደነበረ ነው 8.58፡፡ እንዲሁም እራሱን በሰማይና በምድር መካከል እንዳለ መሰላል አድርጎ ነው 1.51 ይህም በዘፍጥረት 28.10-17 ላይ እንዳለው ነው፡፡ ከዕውርነቱ የተፈወሰው እና ማየትን የተሰጠው ሰው ኢየሱስን አምልኮታል፣ እንዲሁም ቶማስ ኢየሱስን ‹አምላኬና ጌታዬም› ብሎ 20.28 ላይ ጠርቶታል፡፡ ጌታ ኢየሱስ በዚህ ወንጌል ዘገባ ውስጥ ተሰቅሏል፣ ሞቷል፣ እና ደግሞም ተነስቷል፣ እነዚህም ሁሉ ለቁርአን እጅግ ልዩ የሆኑ ወይንም ተቀባይነት የሌላቸው ነገሮች ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ በዚያው በተመሳሳይ ምዕራፍ ውስጥ ሙስሊሞች ስለመሐመድ ትንቢት አለበት በማለት በሚጠቅሱት ውስጥ ኢየሱስ እርሱ ብቻ ወደ እግዚአብሔር የሚወስድ መንገድ እንደሆነ ተናግሯል 14.6፣ እርሱን ያየ ማንም ቢኖር አብን እንዳየ ተናግሯል፣ 14.9. እርሱ በአብ ውስጥ አብ ደግሞ በእርሱ ውስጥ እንደሆነም ተናግሯል፣ 14.11፣ እርሱ ፀሎትን እንደሚመልስ ተናግሯል፣ 14.14፡፡ እኛም በእርሱ ውስጥ የማንኖር ከሆነ ምንም ፍሬ ሊኖረን እንደማይችልም ተናግሯል፣ 15.4፡፡ እኛ እንደዚህ እስልምናን በጣም የሚቃወምን መጽሐፍ ሙስሊሞች ለመጥቀሳቸው በጣም እንደነቅ ይሆናል፣ ይሁን እንጂ ማስታወስ ያለብን ነገር መሐመድ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ እርሱ የተነገሩ ትንቢቶች መኖራቸውን ስለመናገሩ መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለዚህም ሙስሊሞች የተገደዱት የመሐመድን ትንቢት ወይንም ንግግር ሊደግፍላቸው ወይንም ሊያረጋግጥላቸው ይችላል ተብሎ የሚታሰበውን ማንኛውንም ነገር ሁሉ ለመጨበጥ መገደዳቸውን ነው፡፡ ሁለተኛ፡- በዮሐንስ ውስጥ ያሉት ሦስቱ ክፍሎች አፅናኙን የሚገልፁት መንፈስ ቅዱስ ነው በማለት ለይተው ነው፣ (ወይንም የእውነት መንፈስ) በማለት ነው፡፡ ነገር ግን ሙስሊሞች የሚከራከሩት እነዚህ ጥቅሶች ስለ መንፈስ ቅዱስ በምንም ዓይነት አይናገሩም በማለት ነው፡፡ እነሱ እንደሚሉት የትንቢቱ ቃሎች ለመንፈስ ቅዱስ ነው የሚያገለግሉት በማለት ወደ ድምዳሜ እንድምመጣ አያስችሉንም፡፡ ይሁን እንጂ ‹እኔ ባልሄድ አፅናኙ ወደ እናንተ አይመጣም› የሚሉት ቃላት ምንም መግለጫ የማያስፈልጋቸው በጣም ግልጥ የሆኑ ናቸው፡፡ አዲስ ኪዳን የሚለው መጥምቁ ዮሐንስ ገና ከመወለዱም በፊት በመንፈስ ቅዱስ እንደተሞላ ነው፡፡ ከዚያም ስለ ኢየሱስ ሲናገር እርሱ መንፈስ ቅዱስን በእርግብ መልክ እንደተቀበለ ነው፡፡ ስለዚህም መንፈስ ቅዱስ ከኢየሱስ ጊዜ በፊትና በኢየሱስ ጊዜ ሰዎችን ይጎበኝ እንደነበረ ነው፡፡ በመሆኑም የሙስሊሞች ክርክር ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት ነጥብ ሙሉ ለሙሉ በግልፅ ስቶታል፡፡ ኢየሱስ መንፈስ በእነሱ ውስጥ እንደነበረ ያውቃል ... በእናንተ ይኖራልና፡፡ ትንቢቱ ግን መንፈስ በእነሱ ይኖራል ከእነሱም ጋር ለዘላለም ይኖራል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሙሉ፤ ለሙሉ አዲስ ነገር ነው፡፡ እናም መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ውስጥ ስለነበረ ሊሆን አይችልም፣ ትክክልም አይደለም ተብሎ ሊነገር አይቻልም፡፡ ሦስተኛ፡- ከላይ እንዳየነው ሁሉ ጌታ ኢየሱስ የተናገረው አፅናኙ ከደቀመዛምርቱ ጋር ለዘላለም እንደሚሆን ነው፡፡ ስለዚህም መሐመድ ለዘላለም ከእነሱ ጋር መሆንን ቀርቶ ከኢየሱስ ደቀመዛምርት ጋር ሊሆን በምንም ዓይነት መንገድ አይችልም ነበር፡፡ አራተኛ፡- በትንቢቱ መሰረት ዓለም አፅናኙን ሊቀበለው አይቻለውም፣ ምክንያቱም ሊያየው አይቻለውምና፡፡ እጅግ ብዙ ሺ ሰዎች መሐመድን በሕይወት በነበረበት ጊዜ አይተውታል እርሱ ይታይ ነበርና፡፡ ስለዚህም የማይታየው አፅናኝ የሚታየው መሐመድ ሊሆን አይችልም፡፡ አምስተኛ፡- ኢየሱስ ለደቀመዛምርቱ የነገራቸው አፅናኙ አራሱ ከእነሱ ጋር እንደነበረ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከኢየሱስ ደቀመዛምርት ጋር የነበረ ሲሆን መሐመድ ግን ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት ይህ ትንቢት ከተነገረ በኋላ ነበር የነበረው ስለዚህም ከእነሱ ጋር እርሱ ሊኖር አይችልም ነበር፡፡ ስድስተኛ፡- አፅናኙ በደቀመዛምርቱ ውስጥ መሆን ነበረበት፡፡ መሐመድ በኢየሱስ ደቀመዛምርት ውስጥ አልነበረም እንዲሁም ሊሆንም አይችልም፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሌላ ጎኑ ደግሞ አማኞችን በጴንጤ ቆስጤ ቀን ሞላባቸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በክርስትያኖች ሁሉ ውስጥ ይገኛል፡፡ ሰባተኛ፡- ኢየሱስ የተናገረው እርሱ አፅናኙን ከአብ ዘንድ እንደሚልከው ነው፡፡ ሙስሊሞች መሐመድ በኢየሱስ እንደተላከ አያምኑም እነሱም የሚያምኑት መሐመድ በእግዚአብሔር እንደተላከ ነበር፡፡ ስለዚህም ሙስሊሞች ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው በማለት ካላመኑ በስተቀር ይህ ስለ መሐመድ የተነገረ ትንቢት ነው በማለት ሊቀበሉት አይገባቸውም፡፡ በመጨረሻም፡- ከእርገቱ በፊት ኢየሱስ ተከታዮቹ ከጥቂት ቀናት በኋላ በመንፈስ ቅዱስ እንደሚሞሉ ትንቢትን ተናግሮ ነበር ሐዋርያት 1.5፡፡ ወደ አባቱም ከአረገ ከጥቂት ቀናት በኋላ መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ተከታዮች ላይ መጣ፡፡ ‹በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።› ሐዋርያት 2.1-4፡፡ ስለዚህም የዚህ ትንቢት ፍፃሜ የሆነው በጥቂት ቀናት ውስጥ ነበር፡፡ መሐመድ ግን የመጣው ከአምስት መቶ ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ እነዚህን ነገሮች ሁሉ በአንድ ላይ በማስቀመጥ መሐመድ አፅናኙ ሊሆን እንደማይችል እንመለከታለን፡፡ እርሱ ከደቀመዛምርቱ ጋር አልነበረም፣ እርሱ በሐዋርያቱ ውስጥ አልነበረም፣ እርሱ ከእነርሱ ጋር ለዘላለም አልነበረም፣ እርሱ የማይታይ አልነበረም፣ እርሱ በኢየሱስ አልተላከም ነበር እርሱ (መሐመድ) ጌታ ኢየሱስ እንደተናገረው ከተተነበየ በኋላ ወዲያውኑ አልመጣም ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ እውነታዎች የሚያሳዩት በጌታ ከተተነበየው ትንቢት ጋር ሙሉ ለሙሉ የሚገጥመው መንፈስ ቅዱስ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ኢየሱስ አፅናኙን ለይቶ የተናገረው መንፈስ ቅዱስ ነው በማለት ነው፡፡ እርሱም ከደቀመዛምርቱ ጋር ነበር፣ በጴንጤቆስጤም እለት በእነሱ ውስጥ ነበር እርሱ የማይታይ ነበር፣ የመጣውም በፍጥነት ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ በጌታ በኢየሱስ ነበር የተላከው፡፡ እንዲሁም ከክርስትያኖች ጋር ለሁለት ሺ ዓመታት አብሮ ነው ያለው፡፡ እነዚህን ነጥቦች ሁሉ ስንመለከት ሙስሊሞች እነዚህ ጥቅሶች ለመሐመድ ነው የሚያመለክቱት በማለት መናገራቸው በእርግጥ እራሳቸውን የሚያሳፍራቸው ነገር መሆን ይኖርበታል፡፡ |
ዓርብ 13 ማርች 2015
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
አስተያየቶች ለጥፍ (Atom)
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ