ሐሙስ 12 ማርች 2015

ኢየሱስ አሁን አማላጅ ነው ወይ?
ከይስሀቅ አበባየሁ
ፍጥረታትን ከመፍጠሩ በፊት አስቀድሞ በዘላለማዊ ፍቅር በምልዓት የሚኖር እግዚአብሔር ይህንኑ ተቀድቶ የማይደርቅ ተወስዶ የማልቅ አምላካዊ ፍቅር ተጋርተው በእሱ ፍቅር ፀንተው የሚኖሩ ፍጥረታትን ለመፍጠር ወሰነ፡፡ ፍጥረታት የእግዚአብሔር ፍቃድ መገለጫ ናቸውና ፡፡ በመሆኑም ከብዙ ፍቅሩ ከምልዓት ፍቅሩ የተነሳ የምናየውንና የማናየውን ዓለም እግዚአብሔር ፈጠረ፡፡ ከነዚህ ፍጥረት እጅግ በረቀቀ አምላካዊ ግብር በራሱ ሃምሳልና አርዓያ የሰውን ልጅ ፈጠረ፡፡ የሰውን ልጅ ፈጥሮ በልጅነት አክብሮ ከሰማይ በታች ከምድርም በላይ ያለውን ፍጥረት ሁሉ በፀጋ አብዝቶ ለመንግስቱ ተካፋይ አደረገው፡፡ በመልኩና በአርያው የፈጠረውን ሰውን በምድር ሁሉ ላይ ያሉትን ፍጥረታት እንዲዛ ስልጣን ሰጠው፡፡ ነገር ግን ሁሉን ግዛ አስተዳድር ተብሎ የተሾመ አዳም የፈጣሪነት ስሜት እንዳይሰማው የተገዝነት ምልክት ይሆነው ዘንድ መልካሙና ክፉውን ከምታሳውቀው ከዚች ዘፍ አትብላ ብሎ ትዕዛዝ ሰጠው፡፡ የ አዳም ውድቀት አዳም ግን ፈጣሪው የሰጠውን የፀጋ (ስጦታ) ገዚነት አንሶት የባህሪይ አማላክ ሆኖ ለሰማይ ለምድርም ገዚ መሆን ተመኝቶ ዕፀበለስን በመብላቱ ፍጹም ቅጣት ተቀጣ፡፡ ከቦታው ተሰደደ ከማዕረጉ ተዋረደ ሞተ ስጋ ሞተ ነፍስ ለዲያቢሎሰ መገዛትን ያህል ከባድ ቀንበር ተጫነበት፡፡ (ዘፍ1÷2÷3) የአዳም ፀፀትና የእግዚአብሔር ፍርድ ከዚህ በኋላ ባደረገው ስህተት ተፀፅቶ በንስሐ ቢያለቅስ ቢጨነቅ ቢነሳ ቢወድቅ ከዲያቢሎስ ቁራኝነት መቼም ሊላቀቅ አልቻለም፡፡ በስህተቱ ፈፃሚዎች አዳምና ሔዋን ይቅርና ከነሱ የተወለዱ ሁሉ የነሱን መርገም ፍዳ የዘር የሚተላለፈው የዲያቢሎስ ተገዝነት በሁሉ ላይ ሆነ(ሮሜ 5÷12) በሰዋው መስዋዕት በፀለየው ፀሎት ባጠኑት ዕጣን ባቀረቡት ቁርባን(ስጦታ) ከዲያቢሎስ ተገዝነት ነፃ ሊዎጡ አልቻሉም፡፡ስለዚህ ነው ኢሳይያስ "ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ! … ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው"፡፡(ትንቢተ ኢሳይያስ 64÷1-12 ) አነዳዊት በተራቸው "እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም"(መዝሙረ ዳዊት 144÷7) ነብያቱ በአንድ ድምፅ ሆነው ወደ እግዚአብሔር አመለከቱ እንዲህ ያለ አገዛዝም ስለፀናባቸው በሥራቸው መፅደቅ ስለተሳናቸው በዚያን ጊዜ “ ከዲያቢሎስ የባርነት ፃህረኝነት ነፃ የሚያወጣን እርሱ ራሱ ሰው ሆኖ ነው እንጂ ሌላ አማላጅ አስነስቶ ወይም መልአክ ልኮ አይደለም እያሉ ክሶ ማስታረቅ ለክርስቶስ ብቻ የተመደበ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እኛም እንደዚሁ በክርስቶስ ካሳ መዳናችንን አውቀን አምነናል፡፡ በምድር ላይ ጻድቅ መታጣቱ መፃሕፍት ግን ከነአካቴውም “ሕያው ሁሉ በፊትህ ጻድቅ አይደለምና” (መዝ.143:2) ፤ “በዚህም አለም መልካም የሚሰራ ፃድቅ ኅጢአትም የማይሰራ ሰው የለም” (መክ 7፡20) ፤ “ፅድቃችን ሁሉ እንደመርገም ጨርቅ ተቆጠረ” (ኢሳ 63፡6) ፤ “ከርኩስ ነገር ንጹሕን ሊያወጣ ማን ይችላል? አንድ እንኳ የሚችል የለም” (ኢዮ.14:4) እያሉ አስተካክለው ይነግሩናል፡፡ ስለዚህም ሰው ሁሉ በታመነው በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ይፀድቃል እንጂ ከራሱ በምግባሩ ወይንም ከማናቸውም ፍጡር ፃድቅ እንደማያገኝ ኢዮብ ሲያስረዳ “ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ጻድቅስ ይሆን ዘንድ ከሴት የተወለደ ምንድር ነው?”(ኢዮ.15:14) ይላል ፤ ቅዱስ ዳዊትም “በሥራቸው ረከሱ፥ ጐስቈሉ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም። የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ፤ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ። ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም።” (መዝ.14:1-3) ጌታችን ኢየሱስ ሰውን ለማዳን በምድር ላይ መመላለሱ እንዲሁም አማላጅነቱ ዓለም ሁሉ በሠዋው መሥዋእት በፀለየው ፀሎት መዳን እንደተሳነው በሁሉ ዘንድ ከታወቀ ከተረዳ በኅላ አካላዊ ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ያለወንድ ዘር ተፀነሰ ፡ ዲያቢሎስ በዘር ምክንያት በማህፀን ይቆራኝ ነበረ ፡ ቁራኝነት ቀረ ካሳ በማህፀን ተጀመረ፡፡ ሰው ሆነ ስጋ ለበሰ በዚህ ጊዜ በመንፀፈ ደይን ወድቆ አጋንንት ይጠቀጥቁት የነበረ የአዳም ባህርይ ከወደቀበት ተነሳ ከድካሙ ተፅናና በተዋህዶተ ቃል የባሕርይ አምላክ ሆነ ፡ በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ ተቀመጠ፡፡ ተወልዶም 30 ዘመን ሲሞላው በዮሃንስ እጅ ሲጠመቅ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጥሎ የነበረውን አዳም የእዳ ደብዳቤ ደመሰሰልን፡፡ አምላክ ሰው የሆነበት ፍሬ ነገሩ ዲያቢሎስ በወረወራቸው በሶስት ጦሮች በስስት በትእቢት በፍቅረ ነዋይ ተወግቶ ወድቆ ለነበረ ለአዳም ባህርይ ሃይል ለመስጠት ስለሆነ ስራውን በፆም ጀመረ፡፡ መፆሙም በሰውነቱ ነው እንጂ በአምላክነቱ አይደለም፡፡ ክርስቶስም በስስት የመጣበትን በትሕርምት ፡ በትእቢት የመጣበትን በትሕትና በፍቅረ ነዋይ የመጣበትን ንዋይን በመጥላት ግንባር ግንባሩን ብሎ ድል ከነሳው በኅላ መላእክት ሊያገለግሉት መጡ ፤ መላእክት ወደሱ መምጣታቸውም ድል ብትነሱ እንዲሁ መላእክት ወደእናንተም ይመጡላችኅል ሲለን እንደሆነ እናስተውል፡፡ ከዚህ በኅላ ምድረ እስራኤል ገብቶ ትምህርት ተአምራት ጀመረ ፤ መንግስተ ሰማያት በልጅነት ልትሰጥ ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ብሎ አዋጅ ነገር፡፡ኑ ተከተሉኝ እኔ ድል እንደነሳሁ እናንተም ድል ንሱ ብሎ አስተማረ፡፡ ላመኑበትም በመንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሄር ተወልደው የእግዚአብሄር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣን ሰጣቸው፡፡ (ዮሐ 1÷11) 12ቱን ሃዋርያት ፡ 70 አርድእት መርጦ መንግስተ ሰማያት በልጅነት ልትሰጥ ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያላችሁ አስተምሩ ድውያንን ፈውሱ ፡ እናንተን የሰማ እኔን መስማቱ ነው ፡ እኔንም የሰማ የላከኝ አብን መስማቱ ነው ፡ እናንተን እምቢ ያለ እኔን እምቢ ማለቱ ነው ፡ እኔንም እምቢ ያለ የላከኝ አብን እምቢ ማለቱ ነው ብሎ ሾማቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም እነሆ አቤቱ ሁሉን ትተን ተከተልንህ እንግዲህ እኛ ምን እናገኛለን ብሎ ቢጠይቀው ፦ ሰው በሆንኩ ጊዜ የተከተላችሁኝ እናንተ ወልደ እጓለ እምህያው ክርስቶስ በጌትነቱ ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ እናንተም በ12 ወንበሮች ተቀምጣችሁ በ12 ነገደ እስራኤል እንድትፈርዱ እውነት እላችኅለሁ ፡ ብሎ የፍርድ ተካፋዮች አድርጓቸዋል፡፡(ማቴ 19÷16) ከዚህም እልፍ ብሎ ያዘዝኳችሁን ሁሉ ከሰራችሁ ወዳጆቼ እላችኅለሁ እንጂ ባሮቼ አልላችሁም ፡ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅም ለናንተ ግን ካአባቴ የሰማሁትን ነግሬአችኅለሁ አስተምሬአችኅለንና ወዳጆቼ እላችኅለሁ እንጂ ባሮቼ አልላችሁም፡፡ ይህንኑም እኔ በሄድኩበት መንገድ ሔዳችሁ ለአለም የሚኖር ፍሬ ታፈሩ ዘንድ እኔ መርጨ ሾምኳችሁ እንጂ እናንተ የመረጣችሁኝ አይደላችሁም ብሎ ከግብርናተ ዲያቢሎስ ነፃ ከማውጣቱ በላይ አግብርተ ክርስቶስ መባል የክብር ክብር ሲሆን ባሮቼ አልላችሁም ወዳጆቼ እላችኅለሁ በማለቱ የበለጠ የባለሟልነት ማእረግ ሰጥቷቸዋል፡፡ (ዮሐ 14÷17) እንዲሁም “በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም”(ዮሐ.16÷26) ብሎ የእግዚአብሔር ባለሟሎች መሆናቸውን አረጋግጦላቸዋል፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ “አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውከኝ” ባለው ጊዜ ዲያቢሎስ ሩቅ ብእሲ(ሰው) መስሎት በሌሎች እንደለመደ ነፍሱን ከስጋው ለይቶ ስጋውን በመቃብር ነፍሱን በሲኦል ሊቆራኝ ቀረበ፡፡በዚህ ጊዜ ምስጢረ መለኮቱን ብልጭ ቢያደርግበት መላእክት በመስቀሉ ዙርያ ወድቀው ክርስቶስን ሲያመሰግኑት አይቶ ፈራ ደነገጠ ሾልኬ አመልጣለሁ ብሎ ቢቃጣ በነፋስ አውታር በእሳት ዛንጅር አሰረው፡፡በዚህ ጊዜ ሰው ሆኖ ስጋ ለብሶ ድል የነሳኝ ምእመናንን ይነጥቀኝ ዘንድ ስልጣን የተሰጠው ይህ ማነው? ከኔ ህግ ልዩ የሆነ ነፍሳትን ከእኔ እጅ እየማረከ የሚወስድ ይህ ማነው? እንደ ሃጢአተኛ በመስቀል ተሰቅሎ ያለሃጢአት ሞቶ የወደድኩትን እንዳላደርግ የከለከለኝ ልቀርበው የማይቻለኝ ይህ ማነው?ለካስ ሳላውቀው ነው እንጂ እርሱስ ሰማያዊ ነው እያለ ቀባጠረ፡፡ ከዚህ በኋላ ጌታ ነቢያት የተናገሩት ነገር እኔም ሰው የሆንኩበት ምስጢር እንዲህ ዲያቢሎስን ለማሰር ነው፡፡ እነሆ ሁሉ ተፈፀመ ብሎ ክብርት ነፍሱን ከክብርት ስጋው በገዛ ስልጣኑ ለየ፡፡ (ዮሐ 19÷30) በአካለ ነፍስም ከአዳም እስከ ክርስቶስ ያሉ ነፍሳት ታስረው ተግዘው ወደነበሩባት ወደ ሲኦል ወርዶ ግእዛንን ሰበከላቸው ፡ ከቁራኝነት አስለቀቃቸው ወደ ቀደመ ቦታችው ወደ ገነት መለሳቸው፡፡ (1ጴጥ 3÷20)በአፀደ ስጋ ላሉ ሐዋርያትም በዝግ ቤት ገብቶ ቸር አላችሁን? የምስራች አስታረቅኳችሁ አላቸው፡፡ (ሉቃ 24÷36 ዮሐ 20÷20) ፤ 50 ቀን መፅሃፈ ኪዳንን አስተማራቸው፡፡(ሉቃ 24÷25) አብ እኔን ወደዚህ አለም እንደላከኝ እኔም እናንተን ወደአለም እልካችኅለሁና ፡ መንፈስ ቅዱስን በንፍሐት አሳደረባቸው፡፡ እናንተ ይቅር ያላችሁት ሃጢአቱ ይሰረይለታል ፡ ይቅር ያላላችሁት ሃጢአቱ አይሰረይለትም ብሎ በአንብሮተ እድ እስከ ሊቀጳጳስነት ያለውን ማእረግ ሾሟቸው አረገ፡፡(ዮሐ 20÷21 -24) እነዚህ ሁሉ ነገሮች እስከ መስቀል ድረስ ብቻ ናቸው ፡፡ በአጠቃላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰራው እስከ መስቀል የአማላጅነት ስራ ተገብቶ ነው አዳም ከተፈጠረ ግዜ ጀምሮ ሰዎች የሚፈልጉትን ካሣ በመክፈል ስለ ሰው ልጆች ተገብቶ የሚጸልይ የሚለምን የሚማልድ የሚያለቅስ በመጨረሻም ራሱን መስዋዕት አድርጎ በማቅረብ ጌታችን የሰራው ስራ አስታራቂነት ወይም አማላጅነት እንለዋለን፡፡ ይህ ስራ ከዚህ በፊት ያልተፈጸመ ከዛ ቦሃላ የማይደረግ አንድ ግዜ ብቻ የተደረገ ነው፡፡ አንድ ግዜ ካልን ቀራኒዎ ላይ ብቻ ነው ከትንሳኤ ቦሃላ አይከተለውም ከመስቀል ቦሃላ አያማልድም፡፡ ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስ(ከመስቀል ቦኋላ) እንደማያማልድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነበት ምክኒያት በምክረ ሰይጣን ተታሎ በኃጢአቱ ተጎሳቁሎ ኃይሉ ደካማ ሆኖ ተፈርዶበት በመንፈሰ ደይን ወድቆ የነበረ አዳምን ስጋ ለብሶ በበደለው በደል ሁሉ ክሶ የረከሰውን ቀድሶ ያረጀውን አድሶ ኃይሉን መልሶ ፀሎቱ ተሰሚ ተዋግቶ ድል እንዲነሳ አደረገው፡፡ ከማህበረ መላእክት ጨመረው፡፡ በክርስቶስ ካሳ መሆን ይህን ስልጣን ካገኘ በኃላ ያ ተዋርዶ በመንፈስ ደይን(ሲኦል) ወድቆ ጽድቃችን እንደ መርገም ጨርቅ ሆነ ይል የነበረ ሰው ጸሎቱ መስዋዕት ጉዳይ ፈፃሚ ስለሆነለት ቅዱስ ጳውሎስ "እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።" 2ኛ ቆሮ 5÷20 ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ አንደበት ከመስቀል በኋላ ልመና(ምልጃ) ማስታረቅ እንደማይፈፅም ሲያረጋግጥ"በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ(ትማልዳላችሁ) ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን(እንደምማልድ) የምላችሁ አይደለሁም"የሐ 16÷26 በዚያን ቀን እያለ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው ከትንሳኤ በኋላ ያለውን ግዜ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በበኩሉ "ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም።" 2ኛ ቆሮ 5÷16-17 ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስን በስጋው ጾሞአል(ማቴ 4÷1) በስጋው ተርባል(ማር 11÷12) በስጋው ጸልዩአል(ማቴ 26÷36) በስጋው መከራን ተቀብላል(ዕብ 13÷12) በስጋው ማልዶናል(ኢሳ 53÷12) … ወዘተ ያወቅነው ብንሆንም ከዚህ በኋላ ግን እንዲህ በለ ሁኔታ አናውቀውም አለ፡፡ ምልጃም አከተመ አያማልድም የምንለው ቅዱስ ጳውሎስ አስተምሮን ነው ፡፡ "እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤ እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና። ዕብ 7÷26-27" አንድ ግዜ ነው የሚለው፡፡ "ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።" ዕብ 9÷25 አንድ ግዜ ነው የሚለው፡፡ "ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፤ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ" ዕን 10÷11 ይታያችሁ አሁንም አንድ ግዜ ተብሎ ነው የታፃፈው፡፡ አሁን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ አይደለም ፦ ስለምን ቢሉ 1) የሁሉ ነገር አስገኝ እርሱ ነውና - - አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል።ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም።(ዮሐ.5÷21 -22) - - - - ዮሐ.1:3 ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። 2) ምህረትን የሚሰጥ እንጂ የሚለምን አይደለምና - - - ተአምራትን ሁሉ ሲያደርግ እንደ ነብያት “በእግዚአብሄር ስም “ ወይንም እንደ ሃዋርያት “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” አለዚያም “በቅድስት ስላሴ ስም” አላለም ፡ ሁሉን በስልጣኑ አደረገ እንጂ፡፡ 3) መራጭ እንጂ ተመራጭ አይደለም ፡ ሁሉን እንደመረጠ እሱ የሚመረጥ አይደለም ምክንያቱም ለእርሱ ክብሩም ሃብቱም የባህርይው ነውና - - - - ሉቃ6÷13 በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፥ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው - - - ዮሐ.15:16 እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ። - - - ታዲያ የዛሬዎቹ ተረፈ ሉትራን ሳይበቁ በቅተናል ሳያቁ አውቀናል ብለው ዛሬም ኢየሱስ አማላጅ ነው ለማለት የሚቀቅሱትን ጥቅስ እንይ ፩ “ፀሎትንና ምልጃን አቀረበ” ዕብ.5:7 ሲል ምን ማለቱ ነው? እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት - -- ይህ ምን ማለት ነው? ይህ ጥቅስ በማያሻማ ሁኔታ የተገለፀው ነገረ ስጋዌ(እስከ መስቀል ድረስ)ነው፡፡ጌታችን ሊቀ ካህናት ተብሎ ነበርና በስጋው ወራት እንደ ካህናተ ኦሪት የበግና የፍየል ደም ያቀረበ አይደለም፡፡ይልቁንም ፀሎትን እንደላም ልመናንም እንደበግ አድርጎ አቀረበ፡፡ አንድ ጊዜም ስለሆነ ያቀረበው ግዳጅ የሚፈፀም መሆኑን ሲያጠይቅ “ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ” አቀረበ አለ፡፡ “ከሞት ሊያድነው ወደሚችል” ሲልም ሰው ሁሉ በአንድ አዳም እንደሞተና በጌታም በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት በኩል እንደዳነ ስለምእመናን በጌታችን መናገሩ ነው፡፡ “እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት” የሚለው “ወልድ” “በኩር” ሆኖ ሳለ አምላክነት ገንዘቡ ሆኖ ሳለ ፍፁም ሰው በመሆኑ ስለአዳም ያቀረበው ቁርጥ ልመናው ተሰማለት አምላክ ነኝ ልፅልይ አይገባኝም ሳይል ሰው በመሆኑ ታዝዟልና፡፡ ስለመታዘዙም እግዚአብሄርን ስለመፍራቱ ቢል አንድ ነው - - - በአዳም ተገብቶ ነው እንጂ ጌታችን ከመከራ መስቀል በኅላ የሚያማልድ ሆኖ አይደለም፡፡ ፪ "እኔ መንገድ እውነት ህይወት ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም " የሐ 14÷5 ዛሬ በእና ግቢ የተነሱ ልጆችን ከእውነት መስመር ለማስወጣት የሚራራጡ መናፍቃን ከአንደበታቸው የማትለይ ቃል ናት ከላይ ጀምረን ስናነበው ኢየሱስ እያስተማረ ያለው ስለ አማላጅነት ትምህርት ሳይሆን ከአብ ጋር ስላለው የባህሪ ህልውና እና ስለ መንግስተ ሰማያት አወራረስ ነው፡፡ ገና ሲጀምር ቁጥር 1 ለይ "በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም ደግሞ እመኑ" ይላል ህይ ማለት በተለየ አካል በተገለጥኩት በወልድ(ክርስቶስ) በእኔም እመኑ ማለቱ ነው፡፡ ምክኒያቱም ወልድ(ኢየሱስ) ከአምላክነቱ ዝቅ ያለ መስሏቸው እንዳይሳሳቱ ከአብ ጋር በስልጣን በባህሪ አንድ ነውና በእኔም እመኑ አለ፡፡ ለዚህ ነው ወረድ ቁጥር 8 ላይ ብሎ "እኔን ያየ አብን አይቷል፡፡"ያለው በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ "ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው " ያለው ከአብ ጋር ያለው የስልጣን አድነትን ለመግለጽ ነው፡፡ ቁጥር 2 ሲደርስ ደግሞ "በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ" ብሏል ይህ የሚያሳየው የነፍሳችን የደስታ ቦታ እንዳለች ነው፡፡ ምክኒያቱም በማቴ 13÷23 እንደምናነበው ሁሉም ሰው እኩል የነፍስ ቱሩፋት አይፈረጽምም ባለሰላሳ ባለስልሳ ባለመቶነ ፍሬ አለ፡፡ በአባቴ ብዙ መኖሪያ አለ ማለቱ እንደነ ቅዱስ እስጢፋኖስ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጋድሎ የፀኑ ምስክሮች የሚወርሱት ቦታ፡፡ እንደ አብርሃም እንግዳ ተቀባይ የሚወርሱት ቦታ፡፡ እንደ ሐዋርያት ወንጌልን ሰብከው ጽድቅ ተብሎላቸው የሚወርሱት ቦታ፡፡ ታዲያ ይችን የጽድቅ ቦታ ለመውረስ የእግዚአብሔር አምላክነት ጌትነት ገዚነት በተላይም መኖሩን ለማወቅ መንገዱ ኢየሱስ መሆኑን ለመግለፅ ፈልጎ ቁጥር 6 ላይ "እኔ መንገድ እውነት ህይወት ነኝ" አለ እንግዲ እናስተውል እኔ መንገድ ነኝ ያለው አማላጅ ማለቱ አይደለም ቁጥር 2 ላይ "ወደ ምሄድበትስ ታውቃላችሁ መንገዱንስ ታውቃላችሁ" በማለት ጌታ ለሐወርያት መንገዱን ብቻ ሳይሆን ስፍራውንም ጠየቃቸው ቶማስም "ጌታ ሆይ ወደምትሄድበት አናውቅም እንዴትስ መንገዱን እናቃለን "ነበር ያለው ልብ በሉ ሁለት ጥያቄ የያዘ ነው ፡፡ አንደኛ "ወደ ምትሄድበት አናውቅም " ስፍራውና የመጠየቅና ሁለተኛ ደግሞ "እንዴትስ መንገዱን እናቃለን" በማለት ኢየሱስ ወደሚሄድበት ስፍራ አለማወቅን ያስረዳል፡፡ ስፍራው ቅድም እንዳየንው የምንናፍቃት ተስፋ መንግስተ ሰማያት ናት፡፡ አሁን መንገዱስ ነው ጥያቄው ኢየሱስ ይሄድ የነበረው በየሐ 16÷5 መሰረት ወደ አብ ነው፡፡ በመሆኑም ቶማስ የምትሄድበትን(አብን) አናውቅም ባለው ግዜ አብን የትታውቀው በእኔ መንገድነት ነው ሲል" እኔ መንገድ ነኝ" አለ መንገድ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለያየ ትርጉም ቢኖረውም እዚህ ስፍራ ግን የአብ መታወቂያ(መገለጫ) ልጁ ነኝ ማለቱ ነው፡፡ በእርግጥም ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስት ስላሴን ያወቅንበት እውነተኛ መንገድ ነው፡፡ ማለትም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ያወቅንበት መንገዳችን ነው ለምሳሌ በማቴ 3÷16 ላይ ሲጠመቅ "የምወደው ልጄ ይህ ነው" በማለቱ አብ አባትነቱ ታወቀ እህንን ሚስጥር ያወቅንው በኢየሱስ ክርስቶስ መንገድነት ነው፡፡ ቁጥር 6 ላይ ታዲያ" በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም"ማለቱ እኔን መንገዱን ሳያውቅ አብን የሚያቅ የለም ወይም እኔን ተወላዲ ሳያውቅ አብን ማወቅ አይችልም መሆኑን ገለፀላቸው፡፡ ቁጥር 7 ላይ ይህንን ሲያጠናክር "እኔንስ ብታቁኝ አባቴን ባወቃችሁት ነበር፡፡" ማለት ስፍራውን ያላወቁት መታወቂያውን ኢየሱስን አለማወቃቸው እንደሆነ ገለፀላቸው፡፡ እንግዲህ ከላይ በዝርዘር እንዳየንው መንገድ ማለት እንደ ሊፍት የሚያደርስ አይደለም አስተውሎ ምንባቡን ለተረዳው ቶማስ የጠየቀው ስፍራና መንገዱን ያለማወቅ ሁኔታ እንጂ የምልጃን ሁኔታ ፈፅሞ አያሳይም፡፡ ሌላው ከዚህ በጣም ልናስተውለው የሚገባው ነጥብ ጌታ አማላጅ ነው ከተባለ ህይወት ሰጪ እንዴት ሊሆን ይችላል፡፡ ምክኒያቱም አማላጅ ስራው ህይወትን ድህነትን ማሰጠት ነው እንጂ በራሱ አዳኝ አይደለም ኢየሱስ ግን እኔ ሕይወት ነኝ ብላል ስለዚህ አማላጅ ነው ካልን ከቃሉ ጋር እንጋጫለን፡ ፫ “ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ “ ምን ማለት ነው? … ዕብ.12:24 የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል… 1ጢሞ.2:5 አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው …ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛም እውነተኛም የሰውና የእግዚአብሄር መካከለኛ ነው፡፡ ለምን? 1) የነሳው ስጋ የሰው ነውና - - ክርስቶስ አምላክ የሆነ ሰው ፡ ሰውም የሆነ አምላክ ከእርሱ በቀር የለምና “መካከለኛ” የተባለ ወልደ እግዚአብሄር የነሳው ስጋ የሰው ስለሆነ ነው 2) በተዋህዶ አንድ አካል አንድ ባህርይ ሆኗልና - ማቴ 16:16 ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፡- አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። በዚህም በፍፁም ተዋህዶ የሰውና የእግዚአብሄር እንደሆነ አወቅን፡፡ ክርስቶስም እንደሰውነቱ ዘመዳችን እንደአምላክነቱ ፈጣሪያችን በመሆኑ በሰውና በእግዚአብሄር መካከል ያለ መካከለኛ ተባለ፡፡ 3) የብሉይና የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ስለሆነ ነው … በብሉይ የነበረው የላም የበግ - - - መስዋእት በሃዲስ ኪዳን ፍፁም በሚበልጠው በክርስቶስ ደም ተተክቷልና ለብሉይ ኪዳን ካህናትና ለሐዲስ ኪዳን ካህናት አገልግሎትም ሆነ የሹመት ስርአት ፡ ለክህነቱም የስልጣን ልዩነት መካከለኛው ክርስቶስ ነው ፡ ስለዚህም “መካከለኛ” ተባለ፡፡ ፬ "እነርሱም(የብሉይ ኪዳን ካህናት) እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።" ዕብ 7÷25 ቃሉን ለመረዳት በደንብ ገፀ ንባቡን እንመልከት ከዚህ ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን ያሳየናል አሮንን ተከትለው የመጡ ሁሉም ካህናት ማች እንደሆኑ በእነሱ አገልግሎት ፈጽሞ ወደ እግዚአብሔር መንግስት መድረስ እንዳልቻሉ ያሳየናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ ሞት የማያልፍ ክህነቱም የማይለወጥ በመሆኑ አንድ ግዜ ባቀረበው መስዋዕት ስንታረቅበት የምንኖር መሆኑን ያሳያል፡፡ ወንድሞቼ እህቶቼ እናስተውል የዕብራዉያን ጻሐፊ ከላይ እየገለፀ የመጣው የኦሪት ካህናትን አገልግሎት ምን እንደመሚመስል ነበር፡፡ የብሉይ ካህናት ከሌዊ ዘር ተመርጠው በየዕለቱ ድህተት መስዋዕት እናሉ ቢያርዱ ቢሰው የእለት መከራን እንጂ ዘላለማዊ የነፍስ ድህነት ሊያመጣ አልቻለም፡፡ ካህኑ እንካን የህዝቡን ኃጢአት ቀርቶ የራሱን እንካን የዘላለም ህይወት ማስገኘት አልቻለም፡፡ እንግዲህ ካህናት እያገለገሉ በምት ካህናት ሁሉም በሞት እየተነጠቁ እስከ ካህኑ ዘካርያስ በሞት ይነጠቁ ነበር "እነሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለከለከላቸው ካህናት የሆኑ ብዙ ናቸው" ያለው ለዚህ ነው "እርሱ ግን ለዘላለም የማይለወጥ ክህነት አለው" የተባለው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ አለምን አሳልፎ ለዘላለም ህያው ሆኖ የሚኖር ኢየሱስ ነው "ኢየሱስ ትላንትና ዛሬ ዘላለም ያው ነው" ይላል ወንጌል ክህነቱ ከሰው የተገኘ ሳይሆን የባህርይ ገንዘቡ ስለሆነ ዘላለማዊ ካህን ነው፡፡ "እንደ መልከጸዴቅ ለዘላለም አንተ ካህን ነህ ተብሏል፡፡ ዕብ7÷17 ስለዚህ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና አነርሱም የተባሉት እንዳይኖሩ ሞት የከለከላቸው የብሉይ ኪዳን ካህናትን እንጂ ዛሬ እኛን አይደለም ወንጌሉን መላልሰው ያንብቡት ነው መልሳችን፡፡ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ዛሬም ኢየሱስ እየወደቀ የእየተነሳ በሰማይ ያማልዳል ካሉ ሁለት ስህተቶችን ፈፅመዋል አንደኛው ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር የፈፀመው የማዳን ስራ ያላለቀ(incomplete) ነው ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ ኢየሱስ ዕለት ዕለት መስዋዕት እያደረገ ያቀርባል ዕለት ዕለት ይፀልያል እንደማለት ነው ይህ ደግሞ ዘላለማዊ ክህነቱን ምድራዊ ብቻ ማድረግ ነው፡፡ወደ እውነት ተመለሱ መልክታችን ነው፡፡ ፭ የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ሮሜ 8÷34 አንድ ወጪ ወራጁን የሚያስጨንቁበት ጥቅስ ቢኖር ይህ ነው ልብ በሉ በ1938 የታተመው መፅሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ እና የሚፈርደው እንዲሁም 1975 ከግዕዝ ወደ አማረኛ የተተረጎመውም እና የሚፈርደው አሁን ግን በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ያለው ስለ እና የሚማልደው ነው፡፡ እነዚህን 1938 እንዲሁም 1975 መጽሐፍ ቅዱስ በላይብረሪ ገብታችሁ ማንበብ ትችላላችሁ በሮሜ 8÷34 ላይ በተለያዩ ዘመናት የተጻፉ መፅሐፍት ስለ እኛ ይፈርዳል ብሎ ፈራጅ ሲያደርገው በብዝዎች እጅ ላይ የሚገኘው ደግሞ ትርጉሙ አማላጅ ይላል ታዲያ የቅዱስ ጳውሎስ ቃል የቱ ነው ትክክል፡፡ ቁጥር 33 እንዲህ ብሎ ይጀምራል" እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል?" ይላል ይህ የመምረጥ ስልጣን የሚያሳይ ነው ቀጥሎ ደግሞ "የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ(የሚፈርድ) ማን ነው?" በማለት ጥያቄ ይጠይቃል ኮነነ ማለት ሲኦል አስገባ ወይም ገነት አኖረ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፍርድን የመሚያሳይ እንጂ አማላጅነትን ፈፅሞ አይገልፅም፡፡ መኮነን የፈራጅነት ስራ መሆኑን መረዳት ይገባናል፡፡ የሚኮንነው ማነው ብሎ ለጥያቄው መልስ ሲሰጥ የሞተው ትክክል ነው የሚኰንነው ሞቷል፡፡ ይልቁኑ ከሙታን የተነሣው ይላል ሙሉ በሙሉ ትክክል ነው ከሙታን የሚኰንነው ኢየሱስ ተነስታል፡፡ ቀጥሎ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው መቼም እግዚአብሔር ቀኝና ግራ ኁላና ፊት የለውም የማይወሰን ረቂቅ ነው፡፡ ታዲያ የእግዚአብሔር ቀኝ ሲል ምን ማለት ነው በመጽሐፍ ቀኝ ኃይል ስልጣንን ያመለክታል በመዝ 117÷16 ላይ "እግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች " ግልፅ ነው የእግዚአብሔር ኃይሉን የሚያደርገው ሰዎችንን ከፍ ከፍ የሚያደርገው በስልጣኑ በመለኮታዊ ኃይሉ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቀኝ ሲል ስልጣንን (መለኮታዊ ክብሩን) ያመለክታል፡፡ በመቀጠል እንዲህ ይላል ስለ እኛ ¬¬--------ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ፡፡ ክፍት ቦታው ላይ ሙሉ ቢሉን ያለ ጥርጥር የምንሞላው የሚፈርደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ብለን ነው፡፡ ምክኒያቱም ከላይ በዝርዝር እንዳየንው ፈራጅነቱን እንጂ አማላጅነቱን በፍጹም አያሳይም ቃሉ ወደዚህ ወደዛ አያረግም፡፡ ደግሞ "የሚኰንነው ማነው የሚለውና ስለ እኛ የሚማልደው የሚለው ሁለት ቃለት ይጣረሳለው ይጋጫሉ አስማምቶ መተርጎም ተገቢ ነው፡፡የእኛ 81 መጽሐፍ የሚፈርደው ብሎ ነው ያስቀመጠው፡፡እንግዲህ ወንድሞቼ እህቶቼ አሁን ኢየሱስ የሚወድቅ የሚነሳ የሚማልድ አይደለም ምክኒያቱም ቅዱስ ጳውሎስ 2ኛ ቆሮ 5÷16 " ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም።" ተብሎ ተቀምጣልና፡፡ ስለ ፈራጅነቱ ከቅዱሱ መጽሐፍ ማረጋገጫ ሲያርግ እሁን እሱ በክቡር ዙፋን ተቀምቆ የሚፈርድ ነው እንጂ፡፡ መጽሐፍ እንዲህ ይላል ሁላችን "በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና።"ሮሜ 14÷10 "በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና።2ኛ ቆሮ 5÷10 "ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው" ዮሐ 5÷22 "በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ" 2ኛ ጢሞ 4÷1 "የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን አለው።"የሐ5÷27 "ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ።" 1ኛ ጴጥ1÷17 በመጨረሻም "ኢየሱስም፦ የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ አለ።" የዛሬዎቹ ተረፈ አይሁዳዉያንን ከታወሩበት ክህደት ያወጣቸው ዘንድ ኢየሱስ ጌታ ፈራጅ ገዚ ንጉስ አማላክ ብለው ይመሰክሩ ዘንድ ያብቃቸው አሜን፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ